ባለፉት አምስት ወራት ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል-የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አምስት ወራት ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል-የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲሰ አበባ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት አምስት ወራት ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የአምስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የክልል ቢሮ ሃላፊዎችና ተጠሪ ተቋማት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በመድረኩም በስራ ዕድል ፈጠራ፣በክህሎት ስልጠና እንዲሁም በለውጥ ሥራዎች ላይ የክልል ቢሮዎች አፈጻጸማቸውን አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፥ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፥በበጀት ዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ 4 ነ
ጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተይዞ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
ለዚህም ክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ አሰራርን በመዘርጋት፣ለሥራ ፈላጊዎች አስፈላጊው ስልጠና እየተሰጠ ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በየአካባቢው ያሉ ሀብቶችን በመለየት ለስራ ዕድል ፈጠራ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሂደት በመለየት ጸጋን መሰረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዚሁ መሰረት በ2017 በጀት ዓመት እስከ ህዳር ወር ድረስ ለ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
የሥራ ዕድሎቹ የተፈጠሩት በግብርና፣አገልግሎትና ኢንዱስትሪን ጨምሮ በሌሎች ንዑስ ዘርፎች መሆኑን ጠቁመው፥ የስራ ዕድል የመፍጠሩ ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል።
የስራ እድል ፈጠራ ሥራው በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እንዳይስተጓጎል ማይክሮ ፋይናንሶችና ባንኮች ፋይናንስ የሚያቀርቡበት ሥርዐት መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።
ወጣቶች የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ተ
ግባር ማስገባት የሚያስችሉ መርሃ ግብሮች ገቢራዊ መደረጉን ጠቁመው፥ ወጣቶች መሰል ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅመው ወደ ሥራ ሊገቡ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርተው እንዲተኩ የማድረጉ ጅማሬም አበረታች መሆኑን አንስተዋል።
በዘርፉ የሚሰጠው ስልጠና ጥራትን ከፍ ለማድረግም በበጀት ዓመቱ ከ 21 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው፥ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ለ350 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት አምስት ወራት ለ132 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
ወጣቶችን በማደራጀት እና መስሪያ መሬት በመስጠት፣ተዘዋዋሪ ፈንድ አሰራርን በመዘርጋት እና አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም አብራርተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፥ በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት በኮሪደር ልማት፣በከተማ ግብርና፣በዶሮ እርባታና በጓሮ አትክልት ልማት ዘርፎች ውጣቶችን በማደራጀት ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
ሽመናና የቆዳ ሥራዎችን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የክህሎት ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑም አመልክተዋል።
በተለይም የስራ ዕድል ፈጠራው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በክህሎት የዳበረ ዜጋ ለማፍራትም በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጠው ሥልጠና ለውጥን ተግባራዊ ባደረገ መልኩ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የግምገማ መድረኩ እስከ ነገ የሚቀጥል መሆኑንና የክህሎት ልማት፣የስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ላይም ውይይት እንደሚደረግበት ተመላክቷል።