የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሳተፉ መፈቀዱ ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሳተፉ መፈቀዱ ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሳተፉ መፈቀዱ ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከማድረጉም ባለፈ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች የተለያዩ ውጤቶችን እያስገኙ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በተለይም ለረጅም ዓመታት ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበረው የባንክ ዘርፍ ቀስ በቀስ እየተከፈተ መሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋነኛ ማሳያ መሆኑንም ነው የሚያነሱት።
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አረጋ ሹመቴ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ ሆነው መቆየታቸው በሃገሪቱ የምጣኔ ሃብት እደገት ላይ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለግል ባለሃብቶች በተለይም ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መደረጋቸው የላቀ ጥቅም እንዳለው አንስተዋል።
በተለይም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበረው የባንክ ሴክተር ከሀገርም ባለፈ ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑን ነው የገለጹት።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 08 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው በ11ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ያጸደቀ በመሆኑ የውጭ ባለሃብቶች በባንክ ዘርፍ የሚሰማሩ ይሆናል።
በመሆኑም የውጭ ባለሃብቶች በባንክ ሴክተር መሰማራታቸው ዘርፉን በማነቃቃት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከማድረግም ባለፈ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ መሆኑን ዶክተር አረጋ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለውን ጥረት ለማሳካትም ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ምርምር ኮንሰርቲየም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አቢ ከድር፤ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት በባንኮች መካከል የተሻለ ውድድርና የላቀ ውጤት የሚያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም ትልልቅ ዓለም አቀፍ ባንኮች ይዘውት የሚመጡት አቅም የሀገር ውስጥ ባንኮችን የሚያነቃቃና ለተሻለ አገልግሎት የሚያተጋ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባት ለሌሎች ዘርፎችም ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ለግብርና እና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሻለ የብድር አቅርቦት እንዲኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ባንኮችም አሰራራቸውን በማዘመን በሁሉም ረገድ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህም አቅማቸውን ለማጠናከር በመዋሃድ የሰው ሃይል፣የቴክኖሎጂ እና የካፒታል አቅማቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል ብለዋል።
የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መደረጉ ወሳኝ መሆኑን አብራርተው በርካቶች መጥተው መዋለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በሁሉም ረገድ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።