33ኛው የምስራቅ አፍሪካ የመከላከያ እና የፀጥታ ሃላፊዎች መደበኛ ስብሰባ በሩዋንዳ ኪጋሊ አየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ 33ኛው የምስራቅ አፍሪካ የመከላከያ እና የፀጥታ ሃላፊዎች መደበኛ ስብሰባ በኪጋሊ ሩዋንዳ አየተካሄደ ይገኛል።

ስብሰባው እ.ኤ.አ ከዲሴምብር 16 እስከ 21 ቀን 2024 ድረስ እንደሚቆይ ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ክልላዊ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን "የሁለት አስርት ዓመታት ቁርጠኝነት” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይቱን እያካሄደ ይገኛል፡፡

ውይይቱ በቀጠናው መረጋጋትን እና ደህንነትን ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር በሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ የተመራው የኢትዮጵያ መከላከያ ልዑክ በውይይቱ እየተካፈለ ይገኛል።


 

በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት ከኤክስፐርቶች ውይይት በኋላ አጠቃላይ ሪፖርት ለመከላከያ ኤታማዦር ሹሞች እና የፀጥታ ሃላፊዎች ማቅረባቸውም ተጠቁሟል።

በሪፖርቱ ላይ እና በሌሎች ተጨማሪ ሃሳቦች ዙሪያ የምስራቅ አፍሪካ መከላከያ ኤታማዦር ሹሞች እና የፀጥታ ሃላፊዎች እየተወያዩ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ውይይቱ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነትን ለማጠናከር በቁልፍ የደህንነት ጉዳዮች እና ቀጣይ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ማየትና በቀጠናው ባለው ወቅታዊና ወሳኝ የደህንነት ችግሮች ላይ መፍትሄና አቅጣጫ ለማስቀመጥ ወደፊት ለሚደረጉ ጥረቶች ፍኖተ ካርታ እንደሚዘረጋም እንዲሁ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ለክልሉ መረጋጋትና ደህንነት የማዕዘን ድንጋይ በመሆን፣ የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና በአባል ሀገራት መካከል ለክልሉ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ትብብርን ለማጎልበት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱን መቀጠሉም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም