በውጭ አገራት የሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሚያደርጉት ድጋፍ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን እያቃለለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ አገራት የሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሚያደርጉት ድጋፍ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን እያቃለለ ነው
ድሬደዋ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ) ፡-በውጭ አገራት የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች እያደረጉት ያለው ድጋፍ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን እያቃለለ መሆኑን የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
የኢትዮ-ፈረንሳይ አሶሴሽን ፈረንሳይ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያሰባሰበውን 95 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸውን የህክምና መሳሪያዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ዛሬ ለድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር አስረክቧል።
የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ በመላው አለም የሚገኙ የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆች ተደራጅተው እያከናወኑት የሚገኙት በጎ ተግባር ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል ረገድ ወሳኝ አበርክቶ አላቸው።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ምስጋናቸውን በአስተዳደሩና በነዋሪው ስም አቅርበዋል።
በመላው አለም የሚገኙ ተወላጆች እና ወዳጆች በአገርም ሆነ በድሬደዋ የልማት እና የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ይበልጥ ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የድሬደዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው ዛሬ የተደረገው የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎችን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል ።
ዛሬ ለፖሊስ ጠቅላይ መምሪያው የተደረገው ድጋፍ በየትኛውም አጋጣሚና ቦታ ሊከሰት ለሚችል የእሳት አደጋ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ህይወትና ሃብትን ለመታደግ ወሳኝ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የተናገሩት ደግሞ የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የአስተዳደር ልማት ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ውቢት በፍቃዱ ናቸው።
"የድንገተኛ የእሳት አደጋ ቁጥጥር ሙሉ ትጥቅና የመከላከያ ቁሶች ማግኘቱ ከህዝብ ለሚቀርቡ የአገልግሎት ጥያቄዎች ፈጣንና ቀልጣፋ ምላሽ ለመስጠት ያስችለናል" ብለዋል።
የኢትዮ ፈረንሳይ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ሚስተር ሾኪ አሊ ሰዒድ በበኩላቸው በመተባበርና በመተጋገዝ አገርን ወደ ከፍታ ማሻገርና የዜጎችን ማህበራዊ ችግሮች ተቀናጅቶ ማቃለል ወሳኝ ስራ መሆኑን ገልጸዋል ።
በቀጣይም በፈረንሳይ ሆነ በሌሎች ውጭ አገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያን ተወላጆች እና ወዳጆች በማስተባበር በሌሎች አካባቢዎች የሚታዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚተጉም አንስተዋል።
በድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት የአገር ውስጥና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ከድር አልይ ዛሬ የተደረጉት ድጋፎች 95 ሚሊዮን ብር ግምት እንዳላቸው ገልፀዋል።
አሶሴሽኑ ከዚህ ቀደምም 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
የኢትዮ-ፈረንሳይ አሶሴሽን ዛሬ ከለገሳቸው የህክምና መሣሪያዎች መካከል ከ200 በላይ ዘመናዊ አልጋዎች፣ ዊልቸሮች፣ የአልትራ ሳወንድ፣ የፊዚዮቴራፒ፣ የላቦራቶሪ ማሽኖች እና ለጤናው አገልግሎት ግብዓት የሚውሉ ቁሳቁስ ይገኙበታል።
በተጨማሪም ለህፃናት ማሳደጊያ ተቋም የወተት እና የመጫወቻ እንዲሁም ለድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለድንገተኛ እሳት አደጋ ቁጥጥር የተሰጡት የመከላከያ ቁሶች ተጠቃሽ ናቸው።
ድጋፉን የኢትዮ-ፈረንሳይ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ሚስተር ሾኬ አሊ ሰዒድ ለድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ ለጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ እና ለድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ውቢት በፍቃዱ አስረክበዋል ።
በስነ ስርዓቱ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፣ የካቢኔ አባላት ና የህክምና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።