ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች እየሰጠች ያለው አገልግሎት የሚደነቅ ነው - ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን በመቀበል እየሰጠች ያለው የከለላና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች የሚደነቅ መሆኑን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(አይ.ኦ.ኤም) አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ26 ሀገራት የተሰደዱ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስጠለል መሰረታዊ የማኅበራዊ አገልግሎቶችን እየሰጠች ነው።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎትን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 546/2016 ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አቅም በፈቀደ መጠን መሰረታዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ኢትዮጵያ እንደምትሰራ ደንግጓል።

በዚሁ መሠረት ለስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላ መስጠትና ተመላሾች ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ተገቢ የሆነ ህጋዊና ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥራ ወደ ስራ ገብታለች።

የስደተኞችን እና የተቀባይ ማኅበረሰብን ሕይወት በዘላቂነት የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎችም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባባር በፕሮጀክት እየተተገበሩ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በስደተኛ ማዕከላት እና አካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ተጽዕኖ የሚቀንሱ ተግባራት እንዲከናወኑ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በህግ ደንግጋለች።

በዚህም መሰረት ከአንድ ዓመት በፊት በጀኔቫ የስደተኞች ኮንፍረንስ የገባችውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም በአራት ዓመታት 100 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ንቅናቄ ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም ማስጀመሯ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ የምትወጣው ኃላፊነት በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍተኛ እውቅና የተቸረው ነው።

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት(አይ.ኦ.ኤም) ቢሮ ኃላፊ አቢባቱ ዋኔ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዓለማችን በርካቶች በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ለስደት ይዳረጋሉ፡፡

ስደተኞቹን ተቀብለው እያስተናገዱ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት ብለዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመቀበል ምቹ አገልግሎት እየሰጠች መሆኗ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል ዜጎቿ በሙያ ታንጸው ክብርና ደህንነታቸው ተጠብቆ በውጭ የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሀገራት ጋር ስምምነት በመፈራረም እየሰራች መሆኗንም አድንቀዋል።

የኢትዮጵያን ተምሳሌታዊ መንገድ ሌሎች ሀገራት በምሳሌነት በመውሰድ ወደ ተግባር እየገቡ እንደሚገኙም ነው ኃላፊዋ ያነሱት።

በተለያዩ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መንግሥት አበረታች ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት(አይ.ኦ.ኤም) በስደት ዙሪያ የተለያዩ ድጋፎችን ከመስጠት ጀምሮ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል በትብብር እንሰራለን ነው ያሉት ሀላፊዋ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም