ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ሰላምና ፍቅርን በመስበክ ዘላቂ ሰላም የማስቀጠል ሚናችንን ልናጠናክር ይገባል-ቀሲስ ታጋይ ታደለ

ድሬዳዋ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦የሃይማኖት ተቋማት ሰላም፣ ወንድማማችነትና ፍቅርን በመስበክ ዘላቂ ሰላም የማስቀጠል ሚናችንን ልናጠናክር ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተናገሩ።

"ሃይማኖት ለሰላም፣ለአንድነትና ለመከባበር" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በድሬዳዋ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደተናገሩት፥ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለዘላቂ ሰላም በተቀናጀ መንገድ ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው።

የዛሬው ውይይት ለዘመናት የዳበሩ መልካም ግንኙነቶችን በማጠናከር የገጠሙ ወቅታዊ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተለያየ የእምነት ልዩነት ቢኖርም
የእምነት ተቋማቱ በአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ላይ በአንድነት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።


በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን፣ወንድማማችነትንና ፍቅርን ከመስበክ ባለፈ አርአያ የሚሆኑ ሥራዎችን በማከናወን የአገርን ዘላቂ ሰላም የማስቀጠል ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

"እንደሃይማኖት አባት የአስታራቂነት ሚናችንን በአግባቡ በመወጣት ለሰላም መስራት አለብን" በማለትም ቀሲስ ታጋይ ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሼህ ኢብራሂም ኢማም በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የሰላም ምክክሩ በድሬዳዋ የሰፈነውን ሰላም በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ለማስፋት አበርክቶው የጎላ ነው።

ውይይቱ ለቀጣይ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ዕውቀትና ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ማህበረሰቡን በእኩልነት እና በ
ታማኝነት የማገልገል ሃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን ያሉት ደግሞ በምክክሩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።

ከንቲባ ከድር እንዳሉት፤ በመደጋገፍ እና በመቀናጀት የአካባቢና የሀገርን ዘላቂ ሰላም ለማጠናከር ሁሉም በተሰማራበት መስክ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።

በመድረኩ የተሳተፉ የአገር ሽማግሌዎች፣አባ ገዳዎችና ኡጋዞችም ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ማህበረሰቡን የማስተባበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሥራ አስፈፃሚ አባላት፣የሃይማኖት አባቶች፣የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በነገው ዕለት ታላቅ የሰላምና የምስጋና መድረክ በድሬዳዋ ስታዲየም እንደሚካሄድም ታውቋል።

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከድሬዳዋ አስተዳደርና ከድሬዳዋ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም