ቀጥታ፡

የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ለቀጣናው መረጋጋትና ለሶማሊያ ሰላም ለከፈለችው ዋጋ እውቅና የሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና መረጋጋት እና ለሶማሊያ ሰላም ለከፈለችው ዋጋ እውቅና የሰጠ መሆኑ ተገለጸ።

የአንካራው ስምምነት በተፈረመበት ወቅት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሃመድ ባደረጉት ንግግር የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ለችግር ተጋላጭ በመሆኑ በትብብር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት መስጠታቸው ይታወሳል።

ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ውድ የሆነ የህይወት መስዋእትነት በመክፈል ጭምር የኢትዮጵያ ወታደሮች ያደረጉትን የላቀ አስተዋፅኦ በማስታወስ የቁርጥ ቀን ወዳጅ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ፤ የአንካራው ስምምነት ከሁለቱ ሀገራት ያለፈ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር የሚሰሩ አካላትን ተስፋ ያስቆረጠና ቀጣናዊ ትብብርን ያጠናከረ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ስምምነቱ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ጥሩ መሰረት ያኖረና ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ለከፈለችው ዋጋም እውቅና የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የተርኪዬ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ሁለቱ ሀገሮች ተቀራርበው እንዲነጋገሩ ማድረጋቸው የሚያስመሰግን መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር)፤ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት የትብብር ግንኙነትና ወዳጅነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገራቱን ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ የተከናወነ መሆኑን አንስተው ከሁለቱ ሀገራት ባለፈ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ጥሩ መሰረት ያኖረ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ጋር ለሰላምና ልማት በጋራ የመስራት ጽኑ አቋሟን በተግባር ያሳየችበት ፍሬያማ ውይይት መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስኬትና ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም ለቀጣናዊ ትብብር የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑንም ያመላከተ መሆኑን ምሁራኑ ገልጸዋል።

የሶማሊያም የሰላም ፍላጎት ከኢትዮጵያ ጋር ሁለንተናዊ ትብብሯን ለማጠናከር ቁርጠኝነቷን ያሳየ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት የነበራትን የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በምሳሌነት በማንሳት ይህን አቋሟን አሁንም አጠናክራ መቀጠሏን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የልማት እቅዶችና እያከናወነቻቸው ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችም ከራሷ አልፎ በአካባቢው የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን አንስተው ሀገራት በጋራ የመልማት ጥረታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአንካራውን ስምምነት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ጨምሮ በብዙ መልኩ ጥብቅ ትስስር ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም