ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች ያላትን ትብብር ለማጠናከር እየሠራች ነው-አምባሳደር ፈቃዱ በየነ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች ያላትን ትብብር ለማጠናከር እየሠራች መሆኗን አምባሳደር ፈቃዱ በየነ ተናገሩ።

በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈቃዱ በየነ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብት፣ ማህበራዊና ሌሎች ዘርፎች እየተጠናከረ መምጣቱን አስረድተዋል።

ታህሳስ 8/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮ-ታንዛኒያ የመጀመሪያው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የሀገራቱን ግንኙነት ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።

በምጣኔ ሃብት ዘርፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት 49 በረራዎችን ወደ ታንዛኒያ ሶስት ከተሞች በማድረግ ለአገሪቱ ቱሪዝም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ትኩረት ከሰጠቻቸው አምስት የምጣኔ ሃብት ምሰሶዎች አንዱ ቱሪዝም በመሆኑ ፓርኮችን በመገንባትና መዳረሻዎችን በማልማት እያከናወነች ያለውን ተግባር አስታውሰዋል።

ታንዛኒያ በዓመት ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰት ካላቸው የአፍሪካ አገራት አንዷ ስትሆን ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት 17 በመቶውን እንደሚይዝ ጨምረዋል።

በመሆኑም ሁለቱ አገራት በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ልምድ በመለዋወጥ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ አምባሳደር ፈቃዱ ተናግረዋል።

የምጣኔ ሃብት ዲፕሎማሲን ለማጠናከር በንግድ፣ ግብርና እና ሌሎች ዘርፎች እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፥ ኢትዮጵያ በከብት እርባታ ያላትን ተሞክሮ ለመማር ታንዛኒያ መስራት እንደምትፈልግ ጨምረዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር እያከናወነች ባለው ተግባር ከታንዛኒያ ጋር "በተስማማችው ማዕቀፍ" መሰረት እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም 100 ሜጋ ዋት ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የቅድመ ዝግጅት ስራው እየተጠናቀቀ ሲሆን ለቀጣናው ትስስር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

እንደ አምባሳደር ፈቃዱ ገለጻ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም ከኬንያና ታንዛኒያ ጋር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

መንግስት በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት ለመቀነስ የበኩሉን እየተወጣ ሲሆን የክልልና ዞን አስተዳደሮችን የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅ በአፅንዖት አንስተዋል።

በፓን አፍሪካዊ እሳቤ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል የተጀመረው የኢትዮጵያና ታንዛኒያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 60 ዓመታትን ተሻግሯል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም