ቀጥታ፡

በተያዘው በጀት አመት ባለፉት ወራት ከ160 ሺህ በላይ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት አድርገዋል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት አመት ባለፉት ወራት ከ160 ሺህ በላይ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ማድረጋቸውን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች ክብራቸው፣ መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ በህጋዊ መንገድ ወደተለያዩ አገራት ለስራ የሚሄዱበትን ስርዓት መዘርጋቱ ይታወቃል።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ዜጎችን የሙያ ክህሎት በማስታጠቅ በውጭ አገራት የስራ ስምሪት ተወዳዳሪና ተቀባይነት እንዲኖራቸው የጀመራቸው ስራዎች ውጤታማ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ክህሎት መር የስራ እድልን ለመፍጠር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ ዜጎች በውጭ አገራት መብታቸው፣ ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የውጭ አገር የስራ ገበያ በማፈላለግ፣ መዳረሻ አገራትን በመለየትና የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈጸም ዜጎች ህጋዊ የስራ ዕድል እንዲያገኙ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በአገራቱ ያለውን የስራ ፍላጎት በመለየት ተወዳዳሪና ብቁ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዜጎች በቅድሚያ የቁጠባ የሂሳብ ደብተር እንዲከፍቱ በማድረግ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በቆጠቡት ገንዘብ ሀብት አፍርተው ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎችም የስራ እድል እንዲፈጥሩ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ዜጎች የስራ መታወቂያ እንዲኖራቸውና በቂ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የግልጸኝነት ስርዓት እንዲዘረጋ ማስቻሉን ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ከስድስት አገራትና ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈፀም የውጭ አገር የስራ ስምሪት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በተያዘው በጀት አመት ባለፉት ወራት የውጭ አገራት የስራ ስምሪት ያደረጉ ዜጎች ቁጥር ከ160ሺህ  ማለፉን ተናግረዋል።

ዜጎች መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ህጋዊ የውጭ አገር ስራ ስምሪት ስርአትን ተከትለው ሊሄዱ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በደላሎች ተታለው በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገራት ማቅናት ከእንግልት እስከ ህይወት ማጣት የሚያስከትል በመሆኑ ዜጎች ራሳቸውን ከመሰል አደጋ መጠበቅ እንዳለባቸውም ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ የማህበረሰብ አቀፍ ራዲዮ ባለሙያዎች በህገ ወጥ ስደት ላይ እንዲያተኩሩ ስልጠና መስጠቱን በዚሁ ወቅት አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም