የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘን ነው - አርሶአደሮች

አሶሳ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የሚያቀርብላቸው አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂ  ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዳገዛቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የባምባሲ ወረዳ  አርሶአደሮች ተናገሩ።

በምርምር ማዕከሉ ድጋፍ አሲዳማ አፈርን በኖራ እና በተፈጥሮ ማዳበሪያ በመታገዝ የለማ ማሽላ ማሳ ተጎብኝቷል።


 

በባምባሲ ወረዳ የጀማፃ ቀበሌ አርሶአደር ያሲን አይሸላ የምርምር ማዕከሉ አሲዳማ አፈርን በኖራ እና በተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲታከም በማድረጉ  የማሽላ ሰብል እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደር ያሲን የምርምር ማዕከሉ በሰጣቸው 'አሶሳ አንድ' የተሰኘ ምርጥ ዘር ማሽላ በማምረት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላዋ አርሶ አደር ለይላ ናስር በበኩላቸው የምርምር ማዕከሉ በተፋሰስ ልማት እና መሬትን በኖራ በማከም ከዚህ በፊት ምርት የማይሰጥ መሬት አሁን ምርት መስጠት ጀምሯል ብለዋል።


 

''በዚህም ከራስ ምግብ ፍጆታ ባለፈ ለሌሎች አርሶአደሮች ምርጥ ዘር በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነናል'' ሲሉም ነው የተናገሩት።

የምርምር ማዕከሉ በሚያደርገው ዕገዛ ሳይንሳዊ አሰራርን በመላመድ አሲዳማ መሬትን በማከም የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አርሶአደር ፈንታ መለሰ ናቸው።

የሚያመርቱትን ምርጥ ዘር ከአካባቢው አልፎ ለሌሎች አካባቢዎችም ለሽያጭ እያቀረቡ መሆኑን በመጠቆም።


 

የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ደስታ በቀለ በበኩላቸው ማዕከሉ 'አሶሳ አንድ' የተሰኘ የማሽላ ዘር ለአርሶአደሩ በስፋት እያስተዋወቀ እንደሆነ አብራርተዋል።

'አሶሳ አንድ' ማሽላ ዝርያ ተባይን የሚቋቋም እና በሄክታር እስከ 38 ኩንታል ምርት የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል።

ማዕከሉ የተጎዱ የእርሻ ማሳዎችን በማከም አርሶአደሩ የተሻሻሉ የሰብል ዓይነቶችን እንዲያመርት ማድረጉን አቶ ደስታ አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም