ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ የማምረቻ ማሽነሪዎችን መተካት የሚያስችል ምርት እንድናመርት ዕድልን ፈጥሮልናል-አምራቾች

መቀሌ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ የማምረቻ ማሽነሪዎችን መተካት የሚያስችል ምርት እንድናመርት ዕድልን ፈጥሮልናል ሲሉ አምራቾች ገለጹ።

''ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት'' ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃ አስተዋጽኦ እያደረገ በመሆኑ ንቅናቄው መጠናከር እንዳለበትም ተገልጿል።

በመቀሌ ከተማ የማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤት አቶ በረከት ገብረሚካኤል እንዳሉት፥ የፌዴራል መንግስት ለአገር ውስጥ ምርት በሰጠው ትኩረት ዘርፉ እየተነቃቃ ነው።

ከውጭ አገር የሚገቡ ለግብርናና ለኮንስትራክሽን ስራዎች የሚውሉ የማምረቻ መሳሪያዎችን እያመረቱ መሆናቸው ገልፀው፥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማዳን የሚያስችል አቅም እየፈጠርን ነውጨ ብለዋል።

ለአብነትም ምርት ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ የሚውለው መካከለኛ ኮምባይነር ከውጭ ሲገዛ እስከ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ ጠቁመው፤ እርሳቸው የሚያመርቱት ግን ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር እንደሚሸጥ አመልክተዋል።

የዶላር ተመን ማሻሻያ እና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በግብዓት አቅርቦት እና በገበያ ትስስር ላይ ሲያጋጥሙ የቆዩ ችግሮችን እያቃለለ መሆኑን አቶ በረከት ገልፀዋል።

ሌላኛው የማሽነሪዎች አምራች አቶ ሳምሶን ግርማይ፥ በአሁኑ ወቅት እስከ 50 የተለያየ ዓይነት ማሽነሪዎች እንደሚያመርቱ ገልፀው፥ ይህም ከውጭ የሚገቡ ማሽነሪዎች በመተካት የውስጥ አቅምን ማሳደግ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ለእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ የሚውል ማሽነሪ ከውጭ ሲገዛ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚወጣበት ገልጸው፥ በአገር ውስጥ አምርተው እስከ አምስት መቶ ሺ ብር ያህል እየሸጡ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከማዳን ባለፈ ደንበኞች የፈለጉትን የማምረቻ ማሽን በቅርብ እንዲያገኙና ግንዛቤም እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።

የትግራይ የማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር የቦርድ አመራር አባል ዶክተር መብራህቱ መለሰ፥ በክልሉ አንድ መቶ ሰባ የሚሆኑ የማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ገልፀዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ የሚያጋጥሟቸውን የፋይናንስ፣የማስፋፊያ ቦታ፣በዘርፉ የተማረ የሰው ሃይል እና የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት የተቀመጠው አቅጣጫ ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጨምረው ተናግረዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የስራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሙያን በማሳደግ አቅም እየፈጠረ እንደሆነም ዶክተር መብራህቱ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት፣ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ከአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር ዘርፉን በፋይናንስና በክህሎት ለማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም