ቀጥታ፡

የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የብረት መጠለያ በጥንቃቄ ለማንሳት የሚደረገው ጥናት እንደቀጠለ ነው-የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የብረት መጠለያ በጥንቃቄ ለማንሳት የሚደረገው ጥናት እንደቀጠለ መሆኑን የቅዱስ ላሊበላ ደብር ዋና አስተዳዳሪ አባ ህርያቆስ ጸጋዬ ገለጹ፡፡

በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉስ ላሊበላ የተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ለዓለም እያሳዩ እስካሁንም ዘልቀዋል፡፡

አብያተ ክርስቲያናቱ ከዘመኑ የሕንፃ ግንባታ በተለየ ድንቅ በሆነ ጥበብ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ከላይ ወደ ታች እና ከተራሮች ስር ወደ ጎን የተፈለፈሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የዘመናዊ ስልጣኔና የላቀ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ማሳያ የሆኑት የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1970 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት ባህልና ሳይንስ ተቋም /ዬኔስኮ/ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የዓለም ቅርስና የሀገር ሃብት የሆነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ከጎብኝዎችና አጠቃላይ ከቱሪዝም ዘርፉ ከሚገኝ ገቢ እየተዳደሩና ኑሯቸውንም የሚደጉሙ መሆኑ ይታወቃል።


ይሁን እንጂ በአብያተ ክርስቲያናቱ ቤተ መድኃኔዓለም እና ቤተ ማርያም በ2000 ዓ.ም ለአምስት ዓመታት ብቻ በሚል የተሰራው የብረት መጠለያ በቅርሱ ደህንነት ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ደብር ዋና አስተዳዳሪ አባ ህርያቆስ ጸጋዬ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጀምሮ የሰላምና ጸጥታ ችግር የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ጎድቶት መቆየቱን ገልጸዋል።

በጊዜያዊነት ቅርሱን ከዝናብና ፀሃይ ይከልላል በሚል የተሰራው የብረት መጠለያ ሳይነሳ እስካሁንም በመዝለቁ ሌላ ስጋት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በመሆኑም የቅርሱን ደህንነት ለመጠበቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥረት በፈረንሳይ መንግሥት እገዛ መጠለያውን ለማንሳት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በሂደቱ የቅርሱ ጥገና የሚያስፈልጋቸው 24 ቦታዎች የተለዩ መሆኑን አስታውሰው የብረት መጠለያውንም በጥንቃቄ ለማንሳት የሚደረገው ጥናት እንደቀጠለ ይገኛል ብለዋል።

በዘላቂ የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክት መጠለያውን ማንሳት የሚያስችሉ ጥናቶችና የጥገና ስራዎች በጥንቃቄ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስያናት ላይ የተደቀነውን ችግር በትብብር በመፍታት ለቀጣዩ ትውልድ ለማቆየት በልዩ ትኩረት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም በቅዱስ ላሊበላ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የቅርሱን ነባራዊ ሁኔታም ተዘዋውረው መመልከታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም