በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ ሰላምን ከማስፈን ባሻገር ልማትን ለማፋጠን ይረዳል - የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ ሰላምን ከማስፈን ባሻገር ልማትን ለማፋጠን ይረዳል - የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች
መቀሌ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸው በክልሉ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ልማት እንዲፋጠን ያደርጋል ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
በክልሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ ሰላምን ከማስፈን ባሻገር ልማትን ለማፋጠን እንደሚረዳም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።
የመቀሌ ነዋሪው አቶ ገብረመድህን ተስፋይ እንዳሉት፤ ልጆቻችን ትጥቃቸውን አውርደው ወደ ሰላማዊና ልማታዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ መደረጉ ተገቢ ነው።
በአሁኑ ወቅት ትጥቃቸውን የፈቱ የቀድሞ ታጣቂዎች በየማሰልጠኛ ማዕከላት የስነ ልቦናና የሙያ ስልጠና ከመሰጠቱም ባሻገር ድጋፍ መደረጉ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ስልጠናውና ድጋፉ ታጣቂዎቹ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ እንዲያሻሽሉ የሚያነሳሳ መሆኑን በመግለጽ።
አሁን ወደ ማህበረሰቡ እየተቀላቀሉ የሚገኙት የቀድሞ ታጣቂዎች በግብርናና በንግድ ዘርፍ ተሰማርተው ለመስራት የመስሪያ ብድርና መሸጫ ቦታ እንዲያገኙ የፌዴራል መንግስትና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቀጣይ ሥራ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት መብራህቶም ማሞ በበኩሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ በፌዴራል መንግስትና በዓለም አቀፍ ተቋማት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ የስራ እድል አግኝተው ራሳቸው ተጠቅመው በሀገራቸው ልማት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጊዜያዊ አስተዳደሩና ባለሀብቶች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
አቶ አብረሀ ሀጎስ በበኩላቸው፤ ወደ ማሰልጠኛ ማዕከላት ከገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል ልጄ አንዱ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ያሉ ሲሆን ከሰላም እንጂ ከግጭት ትርፍ እንደሌለ በተግባር አረጋግጠናል ብለዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን ያለችው ደግሞ የተሃድሶ ስልጠናውን በመጠባበቅ ላይ የምትገኘው ወጣት ቅድሳን ገብረስላሴ ናት።
የተሀድሶና ማሰልጠኛ ማዕከላት ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ በመስጠት እያስተናገዱ መሆኑም የሚደገፍ ተግባር ነው ብላለች።