ቀጥታ፡

በጌዴኦ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ነው

ዲላ፥ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጌዴኦ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ።

ማህበሩ በዞኑ በሦስት ወረዳዎች በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ200 በላይ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

በማህበሩ የጌዴኦ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድወሰን ዳካ እንደገለጹት ድጋፉ ምግብ ማብሰያና መመገበያ ቁሶች፣ የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች፣ የሌሊት አልባሳት እንዲሁም የአልጋ አጎበርና የውሃ ማከሚያ መድሃኒቶችን ያካተተ ነው።

ድጋፉ በጌዴኦ ዞን ጮርሶና ኮቾሬ ወረዳዎች እንዲሁም በጨለለቅቱ ከተማ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ተደራሽ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ባለፈው መስከረም ወር በወረዳዎቹ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በዞኑ በሚገኙ 18 ቀበሌዎች የመሬት መንሽራተት፣ መሰንጠቅና የጎርፍ አደጋ ደርሶ እንደነበር ተገልጿል።

በዚህም በቋሚና ጊዜያዊ ሰብል እንዲሁም በሃብት ንብርት ላይ ጉዳት መድረሱንና ከአራት ሺህ በላይ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።


ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት በተደረገ ጥረት ተፈናቃዮችን ወደቄያቸው የመመለስና በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያደረገው ድጋፍ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመው፣ መ
ሰል ድጋፎች እንዲጠናከሩም ጠይቀዋል።

በጨለለቅቱ ከተማ የቡኖ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፋንቱ ደቻሳ በበኩላቸው፣ ከአካባቢያቸው ያለው የገላና ወንዝ ሞልቶ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በሃብትና ንብረታቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

በዚህም እሳቸውን ጨምሮ ሰባት የቤተሰብ አባላት ለተረጂነት መዳረጋቸው ነው የገለጹት።

ማህበሩ ጉዳት ከደረሰባቸው ከመስከረም ወር አንስቶ ከጎናቸው መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ፋንቱ፣ ድጋፉ ከነቤተሰባቸው ሕይወታቸውን ለማቆየት እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

ድጋፍ ከተረጂነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ ነው ያሉት ድግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ይስሐቅ ሆጤሳ ናቸው።

የተፈጥሮ አደጋው በተለይ የጎርፍ መጥለቅለቅ ባስከተለው ጉዳት ሳቢያ ለጤና ችግር በመዳረጋቸው የሚሰጣቸው የሕክምና አገልግሎቱ እንዲጠናከር በጌዴኦ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ካሳሁን ሽብሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም