የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣የወንዝ ዳርና የኮሪደር ልማት ስራዎች የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት እንዲቀንስ የጎላ አስተዋጽኦ አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣የወንዝ ዳርና የኮሪደር ልማት ስራዎች የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት እንዲቀንስ የጎላ አስተዋጽኦ አላቸው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣ የወንዝ ዳርና የኮሪደር ልማት ስራዎች የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን ለመቀነስ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
ወደ ከባቢ አየር በሚለቀቁ ሙቀት አማቂ በካይ ጋዞች የተነሳ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነት መቀነስ፣ የምግብ እጥረትና ራስን በምግብ ያለመቻል ችግሮች እየተከሰቱ እንደሆነ ይታወቃል።
የግሪን ሃውስ ጋዞች በተፈጥሯዊ መንገድ ከእንሰሳት እና አትክልቶች የአተነፋፈስ ስርአት ጋር በተያያዘ የሚለቀቁ አልያም በሰው ሰራሽ መንገድ ወደ ከባቢ አየር የሚቀላቀሉ ፤ከፋብሪካዎች እና ተሽከርካሪዎች የሚወጡ ጭሶችን ያካተቱ ናቸው።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ መንግስት የተለያዩ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ የሚያስችል ስራ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
ባለስልጣኑ ከተሰጡት ተግባራት ቀዳሚው የሙቀት አማቂ ጋዞችን መለካት፣ማረጋገጥና ይፋ ማድረግ እንዲሁም የልኬት ትክክለኝነትን በማረጋገጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል የማድረግ ስራ ማከናወን ናቸው ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመሩ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣ የወንዝ ዳርና የኮሪደር ልማት ስራዎች በኢትዮጵያ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን ለመቀነስ አስተዋፆዋቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ስምምነት መፈረሟን ተከትሎ የተለያዩ ሴክተሮችን በማሳተፍ ሂደቱን እየተገበረች መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለይም ከግብርና፣ ከኃይል፣ ማዕድንና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ከመቀነስ አንጻር ያስገኙት አስተዋጽኦ በአግባቡ የመለካት፣ የማረጋገጥና የማሳወቅ ስራ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2030 የሙቀት አማቂ ጋዞችን 68 ነጥብ 8 በመቶ ለመቀነስ ቃል መገባቱን ገልጸው፥ ግቡን ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በእቅዱ አካቶ መስራት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
ይህም የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረጓን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት መቀነስ ለአካባቢ ጥበቃ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ለቱሪዝም እድገትና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በባለስልጣኑ የሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጌትነት አበበ በበኩላቸው እንደገለጹት ያደጉ ከፍተኛ ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመልቀቅ በተፈጥሮ ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡
በተለይም ድርቅ፣ ጎርፍና በርሃማነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
ይህንንም ለመከላከል የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት መጠን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ መለካት፣ማረጋገጥና ይፋ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ባለሙያዎችን የማብቃት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡