ቀጥታ፡

ዴንማርክ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት ትፈልጋለች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ ዴንማርክ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ምጣኔ ሃብት ለመገንባት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ገለጸች።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሰባስቲያን ሉካስ ባች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያና ዴንማርክ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት አንስተዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላት ዴንማርክ የምጣኔ ሃብትና ፖለቲካዊ ግንኙነቷም የበለጠ እየተጠናከረ መምጣቱን አስገንዝበዋል።

ዴንማርክ በተለያዩ የትብብር መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም በጋራ የሚከናወኑ ተግባራት ማሳያ መሆናቸውን አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ምጣኔ ሃብት ለመገንባት በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ዴንማርክና ኢትዮጵያ በግብርና፣ አየር ንብረት ለውጥ፣ ኢነርጅና ሌሎች ዘርፎች በጋራ እየተገበሯቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ማሻሻያ በተለያዩ መስኮች ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከተረጅነት ለመውጣት በፖሊሲ ደረጃ ትኩረት ሰጥታ እየሰራችበት የምትገኘው ልማታዊ ሴፍቲኔትን እየደገፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

መንግስት ለሚያከናውናቸው ድሃ ተኮር የልማት መርሃ ግብሮች ድጋፍ በማድረግ አካታች ምጣኔ ሃብት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉም ጨምረዋል።

ሁለቱ አገራት ያላቸውን የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ትብብርን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ምክትል የሚሲዮን መሪው በአጽንኦት አንስተዋል።

የኢትዮጵያና ዴንማርክ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እኤአ በ1967 የተጀመረ ሲሆን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በፖለቲካ፣ የልማት ትብብርና ሰብአዊ ድጋፍ ላይ እንደሚያተኩር መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም