ፍሪልዮን - ለሀገር ለወገን የሚሰጥ ተመን አልባ ስጦታ - ኢዜአ አማርኛ
ፍሪልዮን - ለሀገር ለወገን የሚሰጥ ተመን አልባ ስጦታ

ግራና ቀኝ እያማትርኩና ውስጤ የሚመላለሰውን ብዙ ሀሳብ መልክ እያስያዝኩ (በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ ወደ ሚገኝ አንድ የኤግዚቢሽን አዳራሽ) ሳዘግም ድንገት ቀልቤን የሚይዝ ጽሁፍ ከባሻገር ተመለከቱ። 'A Frillion Dollar worth Idea' ይላል ጽሁፉ።
ፍሪሊዮን የሚባል ቁጥር መኖሩን ከዚያ ቀደም ሰምቼ ስለማላውቅ፣ ይህ ደግሞ ስንት ነው? በሚል ጉጉት ወደ ኤግዚቢሽኑ ጎጆ ቀረብ አልኩኝ። . . .
ከሩቅ 'ፍሪልዮን' ብዬ ባነበብኩት ሰሌዳ ላይ ያለው ጽሑፍ ቀረብ ብዬ ሳየው 'የትሪሊዮን ዶላር ሀሳብ' ነበር የሚለው። በማላውቀው ምክንያት ለወትሮው የሰማይ ጥግ ሆኖ የሚታየኝ ትሪሊዮን ከማውቃቸው ትንንሽ ቁጥሮች አንዱ ሆኖ ታየኝ። ፍሪልዮን ከሚባለው ቁጥር አንጻር ሁሉም ቁጥሮች ደቃቅ እና ድንክዬ ሆነው ታዩኝ።
ፍሪልዮን የቁጥሮች ንጉስ ሆኖ ታየኝ፤ ቁጥሮች ሁሉ ቁጥራቸውን የሚያገኙበት የቁጥሮች ምንጭና ልኬት። ከሰሌዳው ላይ የተገለጸውን የትሪሊዮን ዶላር ሃሳብ ምንነት እንኳን በቅጡ ሳላጣራ ውስጤን ካነቃው የፍሪልዮን ሀሳብ ጋር እየተጫወትኩ ወዲያ ወዲህ ማለቴን ቀጠልኩ።
ከሚሊዮን ጀምሮ ያሉ ትልልቅ ቁጥሮች የጋራ መለያቸው እና ድንበራቸው '-llion'/'-ሊዮን' የሚለው ድህረ ቅጥያ ሲሆን ትክክለኛ ትርጉሙ ይህ ነው ለማለት ባይቻልም የግዙፍ ቁጥሮች መለያ ሆኖ ያገለግላል። በእርግጥ መጨረሻው ላይ 'ዮን' የሚለው ድምጸት በጣሊያንኛ የብዛት አመልካች ቅጽል ነው።
ከትሪሊዮን ወደ ዜሮ ከዚያም ተመልሼ ወደ ፍሪልዮን ስመጣ ብዙ ጥያቄዎች በፍጥነት ወደ አእምሮዬ እንደ ጅረት ሲፈስሱ ቆዩ። ይህ ሁሉ የሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር። ሀሳብና ምናብ ከጊዜ ውጭ የሚሰሩ የሌላ አለም ክፋዮች ሳይሆኑ የቀሩም። "Free" ነፃ፣ "llion" ደግሞ ደግሞ የቁጥር ታርጋ።
"ፍሪልዮን" ነጻ ቁጥር፤ ነፃን የሚያክል ቁጥር ወሰን የሌለው ነጻ ቁጥር፤ ለሀገር፣ ለወገን፣ ለፈጣሪ የሚሰጥ ተመን አልባ ስጦታ። የፍሪልዮን ዶላር ኢንቨስትመንት፣ በነጻ በመስጠት መክበር። መስጠት - መስጠት - መስጠት።
መስጠት ደማቅ አሻራን አትሞ የማለፍ ትልቅ ምስጢር ነው። በነጻ መስጠት ደግሞ የፍሪልዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ነው። ለዘመናት በገዳ ስርዓት ራሱን ሲያስተዳድር የኖረው የቦረና አርብቶ አደር በነጻ መስጠትን በተመለከተ አንድ አስደናቂ ልማድ አለው።
የቦረና አካባቢ ቆላማ በመሆኑ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞችና ምንጮች እምብዛም የሉትም። ከብቶቹን እና ግመሎቹን ውሃ ለማጠጣት ኤላ ተብሎ የሚታወቅ ጉድጓድ ቆፍሮ ማዘጋጀት ግድ ይለዋል። ኤላ አጠገብ ለእንስሳት የውሃ መጠጫ ገንዳ ይኖራል። የቦረና አርብቶ አደር ውሀውን ከኤላ አውጥቶ እንስሳቱን አጠጥቶ ዝም ብሎ አይሄድም።
እንስሳቱን አጠጥቶ እንደጨረሰ ገንዳውን በውሀ ሞልቶ መሄድ ለዘመናት የቆየ ልማዱ ነው። እንስሳቱ ጠጥተው ከጨረሱ በኋላ ገንዳውን ውሃ ሞልቶ የሚሄዱ ምስጢር ሌላ አይደለም። ውሃ የተጠሙ የዱር እንስሳት እና አእዋፍ በውሀ ጥም እንዳይቸገሩ ውሃን ለዱር ፍጥረታት በነፃ የመስጠት ባህል ነው።
ትልልቆቹ የሰው ልጅ በረከቶች በዋጋ የሚታመኑ አይደሉም። ፍቅር፣ ውበት፣ እውነት፣ እምነት፣ ምስጋና፣ . . . በገንዘብ የምናገኛቸው ነገሮች አይደሉም። ማንም በገንዘብ ድሃ የሆነ ሰው እነዚህን መስጠት ይችላል። ተፈጥሮ እነዚህን ሀብቶች ለሁሉም ሰው የሰጠችው ሁሉም ሰው እነዚህን ኢንቨስት አድርጎ በረከት እንዲሰበስብ ነው።
ሰላምታንና ፈገግታን እንውሰድ። አንድ ሰው ሰላምና ፈገግታ በመስጠት ብቻ የዓለምን ቋጥኞች መናድ ይችላል። ለመስጠት እስከፈለግን ድረስ የምንሰጠው አናጣም። እኛም በነፃ የተሰጠን አለና። ሁሌም መስጠታችንን ለማብዛት እንሞክር። አለም ለማይሰጠጥ ሰው ክብር የላትም። ያለውን ካልሰጠ የሰጠችውን ትነጥቀዋለች።
መስጠት በሌለበት መቀበል ከየት ይመጣል? ከይቅርታ ውጪ ፍቅር፣ ከሰላም ውጭ ደስታ ይኖራል ብለን ማሰብ አንችልም። እርግጥ ነው ዛሬም ቢሆን መግደል ማሸነፍ፣ መጣል መብለጥ በሚመስላቸው አዕምሮዎች ውስጥ መስጠትና ማካፈል፣ ፍቅርና ይቅርታ፣ መጨመርና መሙላት ሳይሆን መቀነስና መጉደል ተደርጎ ይቆጠራል። መስጠት ዞሮና በዝቶ የሚመለስ ብድር ሳይሆን፣ ላይታፈስ ፈስሶ እንደቀረ ውሀ፣ ተቃጥሎ አመድ እንደሆነ ማገዶ ይታሰባል። . . .
. . . መብራቱን፣ ስልኩን፣ ራዲዮውን፣ ቴሌቪዥኑን፣ መኪናውን ወዘተ የሰጠን ሌላ ሰው ነው። ያለሰው ብቻችንን አንድ ቀን እንኳን መዋል አንችልም። በምድር ላይ ሰው ሁሉ ጠፍቶ ብቻችንን ብንቀር ምን የምንሆን ይመስለናል? እንደ አዲስ ድንጋይና ድንጋይ አፋጭተን እሳት እንለኩስ ካልሆነ በስተቀር አሁን ያሉን በረከቶች ሁሉ አይኖሩንም።
ድንጋይ ከማፋጨት የገላገለን አብሮነት ነው፤ መስጠትና መቀበል ነው።
ምሉዕ ሰው መሆን የሚቻለው በመደመር ብቻ ነው። ለብቻ ሰው መሆን የለም። ግለሰብ ሆኖ የቀረ በሞት ይቀጫል፤ ያበቃለታል። "ግለሰብ" ቤተሰብ ከዚያም ህብረተሰብ፣ ማህበረሰብና ሀገረሰብ እያለ ሲበዛ ሞት የማያቆመው ችግር የማይረታው የሰውነት ምስጢር ይገለጣል፤ ምሉዕ ህይወት በፍሪልዮን ብቻ ትለካለች።
ምንጭ:- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመደመር መንገድ መጽሀፍ (ገጽ 327 - 339)