ግዙፉ የሕንድ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ አሾክ ሌይላንድ በኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ግዙፉ የሕንድ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ አሾክ ሌይላንድ በኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ የሕንዱ ግዙፉ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ አሾክ ሌይላንድ በኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ።
በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሃ ሻወል አሾክ ሌይላንድ ኩባንያን ካቀፈው የሂንዱጃ ግሩፕ ሊቀመንበር ፕራካሽ ሂንዱጃ ጋር የተወያዩ ሲሆን በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ገልጸውላቸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሰፋፊ የገበያ ዕድሎች አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያደረገቻቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ፈጠሩትን ምቹ ዕድልም ጠቅሰዋል።
የሂንዱጃ ግሩፕ ሊቀመንበር ፕራካሽ ሂንዱጃ በበኩላቸው ከኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ የሚያስችል ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።
ለውጭ አልሚዎች ምቹ ዕድል ለመፍጠር ኢትዮጵያ ያደረገችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም አድንቀው፤ ይህም ለኩባንያው ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር መግለጻቸውን በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በሂንዱጃ ግሩፕ ባለቤትነት የሚተዳደረው አሾክ ሌይላንድ እ.አ.አ በ1948 የተቋቋመ ሲሆን በሕንድ ሁለተኛው ግዙፍ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።