አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ብልጽግና እንዲረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች።
ይህን የገለጹት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ተጠባባቂ ምክትል የሚሲዮን መሪ ናዮሚ ፌሎስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት በአፍሪካ ትልቅ ትኩረት ከምትሰጠው አጋርነት መካከል ተጠቃሽ መሆኑን አስታውቀዋል።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርት፣ በጤና፣ በሰብዓዊ ድጋፍና በሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በትብብር እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እድል መኖሩን ጠቅሰው ይህንን እድል በመጠቀም በርካታ የአሜሪከ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድና በቦይንግ ኩባንያ መካከል ለበርካታ ዓመታት የቆየውን የኢንዱስትሪና የቴክኒክ እንዲሁም የአቪዬሽን ልማት ለማሳያነት ጠቅሰዋል።
በቢዝነስ አጋርነት በኩልም በተለይም በዳያስፖራው የሚከናወን መልከ ብዙ ኢንቨስትመንቶች እንዳሉ አንስተዋል።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ዲፕሎማሲያዊ ተደማጭነትና ሽብርተኝነትን የመዋጋት ልምዷን በማውሳት፤ ያለ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት መፍጠር እንደማይቻል ነው የገለጹት።