ኢትዮጵያ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷን እያሳደገች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷን እያሳደገች ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት አቅርቦት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷን እያሳደገችና በዘርፉ ያላትን ገጽታ እየገነባች መምጣቷን የኢትዮጵያ ቅባትና ጥራጥሬ እህሎች ማህበር አስታወቀ፡፡
በጥራጥሬና የቅባት እህሎች ኢንቨስትመንት ዙሪያ ያተኮረ ምክክር ዛሬ ተካሂዷል፡፡
በምክክሩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሐብረቢን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ላኪዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሐብረቢ በዚሁ ወቅት መንግስት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ግብርናን ለማሳለጥ የሚረዱ አስቻይ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ተግባራዊ መደረጉ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችንና ማነቆዎች መፍታት ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
ይህም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አመልክተዋል
ኢትዮጵያ የአለም የንግድ ስርዓት ውስጥ ለመግባትና የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ተዋናይ ለመሆን እየተዘጋጀች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሂደቱ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ያላትን የንግድ እንቅስቃሴ ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸው በተለይም በግብርና ወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ላኪዎች ምርቶች ላይ እሴት መጨመር ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቅባትና ጥራጥሬ እህሎች ማህበር ስራ አስኪያጅ ኤዳኦ አብዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጥራጥሬና የቅባት እህል ምርትን ለውጪ ገበያ በማቅረብ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እየሆነችና በዘርፉ ያላትን ገጽታ እየገነባች መምጣቷን ጠቅሰዋል፡፡
ማህበሩ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መሰራቱ ለተገኘው ውጤት ወሳኝ ሚና መጫወቱን በማንሳት በቀጣይም በመንግስት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በምክክር መድረኩ በጥራጥሬና በቅባት እህል ዘርፍ ላይ የተሰራ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡