ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለው ሀገራዊ ምክክር ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምንድን ነው? - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለው ሀገራዊ ምክክር ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምንድን ነው?
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በምክክርና በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየመከረች መሆኑ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አዘጋጅነት “የሚዲያ ሚና በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደት” በሚል መሪ ሃሳብ በጉዳዩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረ አረጋዊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ለአገራዊ ምክክሩ መገናኛ ብዙሃን የላቀ ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን በመጠቀም፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮቿን በውይይት በመፍታት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በጀመረችው ታሪካዊ እርምጃ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ወሳኝ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል።
በአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ምሁሩ አብዲሳ ዘርዓይ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ ምክክር ሂደት ያላቸው ዕድልና ስጋቶችን አቅርበዋል።
መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር አወንታዊ ሚና የመጫወት ዕድል ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።
በተለይም በሂደቱ አፍራሽና ሴራ የተሞላባቸውን አካሄዶችን ከመጠለፍ ይልቅ ሚዲያው ዕውነታ ላይ የተመሰረተ መረጃን ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህርት ሕይወት ዮሐንስ በበኩላቸው ከሰብአዊ መብት፣ መልካም አስተዳደርና የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልባት የሚዲያን ፋይዳ ጠቅሰዋል።
ባለሙያው እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ በማሰብ ከግጭት አቀጣጣይ ይዘቶች ይልቅ አወንታዊና ገንቢ እሳቤዎች ላይ ማተኮር ይገባል ባይ ናቸው።
በተለይም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ግጭት አባባሽ ዘገባዎችን ከመስራት መቆጠብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ሙያተኞችም በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት የሚደረገው ጥረት እንደሚያግዙ አረጋግጠዋል።
የምክክር ሂደቱም አሳታፊነቱን ጠብቆ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌቱ(ዶ/ር) የሀገራዊ ምክክር ሒደቱ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን ግንዛቤ በመፍጠር የሚጫወቱትን ሚና አበረታተዋል።
በዚህም ብሔራዊና የህዝብ ጥቅምን በማስቀደም በግንዛቤ ፈጠራ ጎን ለጎንም አጀንዳ በማደረጃት ለሀገራዊ ምክክሩ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
