ቀጥታ፡

መንግስት ወጣቶች የዲጂታል ቢዝነስና የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል - አቶ ሰለሞን ሶካ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንግስት ወጣቶች የዲጂታል ቢዝነስና የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሶለሞን ሶካ ገለጹ፡፡

የሴቶችና የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ፎረም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

ፎረሙ አፍሪካውያን ሴቶችና ወጣቶች በፍጥነት እያደገ ከሚገኘው ዲጂታል ኢኮኖሚ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡


 

በፎረሙ መክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የሴቶችና የወጣቶችን ተሳታፊነት ዕውን ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋና ሰፊ የወጣት ቁጥር ተጠቅማ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የሴቶችና የወጣቶችን ተሳታፊነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ወጣቶችን የዲጂታል ቢዝነስና የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ከግል ዘርፎችና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያውያን ኢንተርፕሪነሮች ስኬታማነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን መከወን የሚያስችሉ ዕቅዶች መነደፋቸውን አብራተዋል፡፡


 

በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማሳደግና በማስፋት ረገድም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አበረታች የሆኑ ተሞክሮዎችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የሴቶችና ወጣቶች የፋይናንስ ተጠቃሚነት በ2030 ሙሉ ለሙሉ እውን ለማድረግ የተያዘው ዕቅድም( WYFIE 2030) ሆነ አፍሪካውያን በጋራ የሚገበያዩበት ዲጂታል ፕላትፎርም(Sokokuu-Africa) ለማልማት እየተደረገ ካለው ጥረት ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

የአፍሪካውያን ሴቶችና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ከሚደረገው ውይይት ጎን ለጎን ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽንና ባዛር መካሄዱ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም