ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ የጥራት ደረጃቸው የተጓደለና ጊዜ ያለፈባቸው የምግብና ጤና ግብዓቶችን ይዘው በተገኙ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገለጸ

ጅማ፣ታህሳስ10/2017(ኢዜአ)፦ የጥራት ደረጃቸው የተጓደለና ጊዜ ያለፈባቸው የምግብና የጤና ግብዓቶችን ይዘው በተገኙ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በምግብና ጤና ግብዓቶች ቁጥጥርን በተመለከተ የባለ ድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በጅማ ከተማ ተካሂዷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ እንደገለፁት፤ ንፅህናቸው የተጓደለ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች በህብረተሰብ ጤና ላይ የከፋ ጉዳት አላቸው።

በዚህም ችግሩን ለመከላከል ባለስልጣኑ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከፌድራል ፖሊስ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 59 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ጥራቱን ያልጠበቀ ምግብ እና 168 ሚሊዮን ብር የሚገመት የጤና ግብዓቶች መያዛቸውን ገልጸዋል።

ድርጊቱን ፈጽመው በተገኙ ተቋማት የፍቃድ ስረዛ፣ የማሸግና የእገዳ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ከዚህም መካከል 156 መድኃኒት ቤቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

በጅማ ጉምሩክ ጽህፈት ቤት የሕግ ተገዥነት ምክትል ስራ አስኪያጅ ምክትል ኮማንደር ታደለ ዮሀንስ፤ በተያዘው ዓመት ፅህፈት ቤቱ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው መድኃኒት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተናግረዋል።

በዚህም 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ ሂደት ላይ ነው ብለዋል።

በፌዴራል ፖሊስ የጅማ ቅርንጫፍ የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ ናስር በበኩላቸው፤ በኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ መድሃኒት ዝውውር ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በተከናወነው ቅንጅታዊ አሰራርም በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የጤና ግብዓቶች እየተያዙ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም