የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ጋር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ጋር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ደኀንነቱ የተጠበቀ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተፈራርመዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት ሁለቱ ተቋማት በተሻለ ግንኙነትና ትብብር የባቡር ትራንስፖርት ዘርፉን ሰላምና ደህንነት የበለጠ ለማስጠበቅ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል።፡
ፖሊስ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመከላከል ከፍተኛ ኃላፊነት በመውሰድ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይም የተጀመረው ወንጀል የመከላከል ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው የሀገራችን አካባቢዎች ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እና ሕብረተሰቡን በማስተባበር፤ መረጃን በመለዋወጥ ፀጥታን በማስከበር፣ የትራፊክ ደኅንነት በማሳለጥ እና በመሠረተ ልማቱ ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል በቅንጅት ለመሰራት ስምምነቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ስምምነቱ በቀጣይ የሎጀስቲክ ድጋፍ ለማድረግ እና በአቅም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት የቴክኖሎጂ አቅሞችን በመጠቀም የጥበቃና ደኅንነት ሥራዎችን ለመሥራት፣ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ፣ የሎጀስቲክ ድጋፍ ለማድረግ፣ በሰው ሃይል ትምህርትና ስልጠናዎች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡