የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል- ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል- ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
ታርጫ፤ ታህሳስ 10/2017(ኢዜአ)፦ በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለፁ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ አንደኛ ዙር የትምህርት ዘርፍ ጉባዔ "የትምህርት ጥራት እመርታ ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ በታርጫ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር እና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችን ጨምሮ አመራሮችን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ የነገ ሀገር ተረካቢ፣ ብቁና ምክንያታዊ ዜጋ ለማፍራት የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመሆኑም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በየደረጃው በትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶች ውጤት እያስገኙ መሆኑን ገልጸው፤ በትምህርት ተደራሽነት የማስፋት፣ ግብዓት ማሟላትና ጥራት የማስጠበቅ ስራዎችን ህብረተሰቡ መደገፍ እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በዚህም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነትና ጥራት ችግርን የመፍታት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂ የማደራጀትና የመምህራንን አቅም ማጎልበት ላይ በቀጣይነት እንደሚሰራበት ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፣ "ትምህርት ውጤት የሚያመጣው ጥራቱና ተገቢነቱ ሲረጋገጥ ነው" ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በትምህርት ተደራሽነትና ፍታሐዊነትን የማረጋገጥ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም በትምህርት ጥራት ግን ውስንነቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።
በዚህም ትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ጉድለት መንስኤዎችን በመለየት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ተግባራዊ በተደረጉ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሀ ግብሮች ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እንደተገኘ አንስተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የመምህራን አቅም ግንባታ እና የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በትምህርት ለትውልድ ፕሮጀክት ከ434 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በገንዘብ፣ በጉልበትና በአይነት ከህብረተሰቡ በማሰብሰብ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና ጥገና ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።