ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ መገናኛ ብዙሃን ለሀገራዊ ምክክር ሂደት መሳካት ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩ ጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2017 (ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም ለሀገራዊ ምክክር መሳካት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት “የሚዲያ ሚና በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን” በሚል መሪ ሀሳብ አገራዊ ውይይት እያካሄደ ነው።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌቱ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ቀጣይነት፣ ለችግሮች መፍትሔ፣ ሰላምና መረጋጋትን በጽኑ የሚፈልጉ መሆናቸውን በምክክሩ ሂደት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ ታይቷል።

ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን የምክክሩን አስፈላጊነትና ምንነት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር እያደረጉ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀጣይም ብሔራዊና የህዝብ ጥቅምን በማስቀደም ገለልተኛ በሆነ መንገድ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠርና ከማስተማር ጎን ለጎን አጀንዳቸውን በማደራጀት ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

በውይይቱ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎች፣ ሙያተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ሀገራዊ ምከክሩን ከማሳለጥ አንጻር የመገናኛ ብዙሃን ሚና ላይ ያተኮሩ ጽሆፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም