የኢንዱስትሪ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ኢንቨስትመንት በማሳለጥና በዕውቀት ሽግግር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው- ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ኢንቨስትመንት በማሳለጥና በዕውቀት ሽግግር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው- ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/ 2017 (ኢዜአ)፡-የኢንዱስትሪ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ኢንቨስትመንት በማሳለጥና በዕውቀት ሽግግር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው በቻይና ባለሃብቶች የለማውን የሁዋጂን ኢንተርናሽናል ላይት የኢንዱስትሪ ሲቲ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን ጎብኝቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ ሙሉ ይርጋ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው የኢንቨስትመንት ሥራ የሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚው ዘርፉ የጋር ዕድገት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ኢንቨስመንት በማሳለጥና በዕውቀት ሽግግር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንዳለ አንስተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በቀጣይም የዕውቀት ሽግግር በመፍጠርና ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ ዞኑ የሚገኙ ፋብሪካዎች ተኪ ምርቶችን ላይ እንዲያተኩሩ አስገንዝበዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በጋር እና በትብብር በመስራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማቅረብ ይጠበቃልም ነው ያሉት።
የሁዋጂን ኢንተርናሽናል ላይት የኢንዱስትሪ ሲቲ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ፕሬዚዳንት ዛንግ ሁዋሮንግ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ዕድገት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር ተፈሪ መለስ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን በመጠቀም ለጎረቤት ሀገራት ምርቶችን በመላክ ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከነዳጅ ወደ ታዳሽ ኃይል የሚለውን የመንግስት ፖሊሲ በመከተልም የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም ኩባንያው በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡