ያለ ደረሰኝ ሲነግዱ በተገኙ 1 ሺህ 145 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ያለ ደረሰኝ ሲነግዱ በተገኙ 1 ሺህ 145 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 10/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ያለ ደረሰኝ የሚካሄደውን ንግድ ለማስቀረት በሚደረገው ቁጥጥር 1 ሺህ 145 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
መንግስት አገርን ለመገንባት፣የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን በሚያደርገው ጥረት ዋነኛ የገቢ ምንጩ ከዜጎች የሚሰበሰበው ታክስ ነው፡፡
በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ታክስና ግብር መክፈል ዋነኛ መሰረት ቢሆኑም አንዳንድ ህገ ወጦች በሚያከናውኑት ያልተገባ ተግባር ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት መንግስት ተገቢውን ገቢ ማግኘት እንዳልቻለ ይነገራል፡፡
ይህን ተከትሎ በአዲስ አበባ ያለደረሰኝ የሚካሄደውን ሽያጭ ለማስቀረትና መሰብሰብ የሚገባውን ገቢ ለመሰብሰብ በከተማ አስተዳደሩ የሚመራ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ የቁጥጥርና ክትትል ተግባር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካትና ያለደረሰኝ የሚካሄደውን ግብይት ለማስቀረት እያደረገ ባለው ተግባር ዙሪያ ኢዜአ ከቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ አበባ ሰፊ የገቢ አቅም ያላት መሆኑን ተከትሎ መሰብሰብ የሚገባውን የገቢ አቅም አሟጦ ለመሰብሰብ የተለያዩ የገቢ መሰብሰቢያ አማራጮች መዘርጋታቸውን አብራርተዋል፡፡
ይህም ወደ ታክስ መረብ ያልገቡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ባርና ሬስቶራንት፣ስጋ ቤቶች፣አከራይና ተከራዮችን ወደ ታክስ መረብ የማስገባት ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡
በከተማው ያለደረሰኝ የሚካሄደውን ንግድ ለማስቀረትና ከተማ አስተዳደሩ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ለመሰብሰብ በከተማ አስተዳደሩ የሚመራ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ቁጥጥር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በዚህም ባለፈው ህዳር ወር ብቻ 1ሺህ 145 ነጋዴዎችና ድርጅቶች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲያካሄዱ ተገኝተው እርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቀዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ገቢ መሰብሰቢያ አማራጮች 230 ነጥብ አራት ቢሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አቶ ሰውነት ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ የገቢዎች ቢሮ ባለፉት አምስት ወራት 81 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 72 ነጥብ 45 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡