በቡና ግብይት ሥርዓቱ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ውጤት አስገኝቷል-የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በቡና ግብይት ሥርዓቱ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ውጤት አስገኝቷል-የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 9/2017( (ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት በቡና ግብይት ሥርዓቱ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ውጤት ማስገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገለጹ።
የቡና ግብይት እሴት ሰንሰለቱን በማሳለጥና በበቂ መረጃ በማስደገፍ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል።
ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ብሔራዊ የቡናና ቅመማ ቅመም አውደርዕይ በሀዋሳ ከተማ ተከፍቷል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ ባለፉት አራት ዓመታት በቡና ግብይት ሥርዓቱ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ውጤት አስገኝቷል።
የቡና ግብይት እሴት ሰንሰለቱን ለማሻሻል በተሰራው ሥራ የተገኘውን ውጤት ቀጣይነት ለማረጋገጥም አሰራሩን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአውሮፓ ህብረት የጸደቀው የግብይት ደንብ ቡናው የተመረተበትን ቦታና አጠቃላይ መረጃ ለማወቅ በጂኦሎኬሽን የተደገፈ አሰራር በቀጣዩ ዓመት እንደሚተገበርም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
በዚህም ከአርሶ አደሩ ጀምሮ በቡና ግብይት የሚሳተፉ አቅራቢዎችና ላኪዎች የእሴት ሰንሰለቱን የሚገልጽ አሰራር ካልተከተሉ የቡና ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደማይችሉም ገልጸዋል።
አዲሱ አሰራር እያንዳንዱ አምራች፣ አቅራቢና ላኪ በበቂ መረጃ እንዲንቀሳቀስ የሚያስገድድ በመሆኑ የዘርፉ ተዋንያን በቂ ዝግጅት በማድረግ የግብይት ሰንሰለቱን ለማጠናከር መስራት አለባቸው ብለዋል።
አውደ ርዕዩም የአምራቹን፣ የአቅራቢውንና የላኪውን ትስስር በማጠናከር ግብይቱን ለማሳለጥና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያበረታታ መሆኑን አስረድተዋል።
ተመሳሳይ አውደ ራዕዮች በጅማና በድሬዳዋ እንደሚካሄዱ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የቡና ግብይት ሥርዓቱ በበቂ መረጃና ቴክኖሎጂ የተደገፈና መነሻና መድረሻው የታወቀ የሚያደርጉ አሰራሮች እየተዘጋጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሲዳማ ክልል እርሻ ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው፥ የቡናና ቅመማ ቅመም አውደ ርዕይ የግብይት ስርዓቱን ለማሳለጥ አቅም የሚፈጥር ነው።
በክልሉ 264 አርሶ አደር ላኪዎች እና 443 አቅራቢያዎች እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን እንዳሉ ጠቅሰው፥ የአውደ ርዕዩ ሃዋሳ ላይ መከፈት ለክልሉ ትልቅ እድል ነው ብለዋል።
ከአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች መካከል ከሲዳማ ክልል ዳራ ኦቲልቾ ወረዳ የመጡት ቡና አቅራቢ ወይዘሮ ገነት ፍቅሬ በአውደ ርዕዩ ለሁለተኛ ጊዜ መሳተፋቸውን ገልጸው፣ይህም ከላኪዎችና ወኪሎች ጋር የመገናኘት እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ የተሳተፉት አርሶ አደር ስለሺ ዶጌ በበኩላቸው በ2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬታቸው ላይ ጥራት ያለው ቡና በማምረት የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
አውደ ራዕዩም ከላኪዎችና አቅራቢዎች ጋር የመገናኘት እድል በመፍጠር የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረው፣ በመድረኩም ቡናቸውን እያስተዋወቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው አውደ ርዕይ ላይ ከአራት ክልል የተውጣጡ 300 የሚደርሱ ቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።