ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማት የበኩላቸውን ወሳኝ ሚና እንዲወጡ ሰላም ሚኒስቴር ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማት የበኩላቸውን ወሳኝ ሚና እንዲወጡ ሰላም ሚኒስቴር ጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ)፦ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማት የበኩላቸውን ወሳኝ ሚና እንዲወጡ የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ ጥሪ አቀረቡ።
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂዎች እና የተቋሙ የስራ ሃላፊዎች ጋር ትውውቅ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት የሃይማኖት ተቋማት የሚያከናውኗቸው ተግባራት ሀገራዊ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ የብዝሃ-ሃይማኖት አማኒያን ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በዚህ ነባራዊ ሁኔታ መንግስት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጣልቃ ሳይገቡ በትብብርና በቅንጅት ከምንጊዜውም በላይ ስለሰላም አብረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ጥሪዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ በተለይም ችግሮች በምክክርና በውይይት እንዲፈቱ በማድረግ የማይተካ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።
በዚህም የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ እየፈታን ለነገው ትውልድ ሰላማዊና የበለፀገች ሀገር ለማስረከብ ዛሬ ትልቅ የጋራ ኃላፊነት አለብን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባቶችና የስራ ኃላፊዎች ከሚኒስቴሩ ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ሰላም ግንባታ ሂደት የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ገመግለጻቸውን ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።