ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምትከተለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተቀባይነት እያገኘ ነው

ጂንካ፤ ታኅሳስ 9/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምትከተለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኩሴ ጉድሼ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነታቸውን በሠላም እንዲፈቱ ከማድረግ ባለፈ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባህሏን ለዓለም ያሳየችበት ነው።


 

በሁለቱ አገሮች የተደረሰው ስምምነትም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እውን ለማድረግ፣ ለቀጣናው ሰላም፣ በጋራ ለማደግና ለመልማት ለሚደረገው ትስስር የጎላ አስተዋጽኦ አለው።

በጂንካ ዩኒቨርሲቲ "የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥረት እስከ አንካራ ስምምነት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ የምሁራን የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን እያደረገች ያለው ጥረት ብሄራዊ ጠቅሟን ለማስከበር የምታነሳቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት እንዲያገኙ አድርጓል።

በተለይ በቅርቡ በአንካራ የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር አብሮ ለማደግና ለመበልፀግ ያላትን ፅኑ ፍላጎት በግልጽ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት እንዲሳካ ሕዝቡ በሚችለው ሁሉ ማገዝ እንዳለበት ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት እያደረገች ያለችው ጥረትና በሂደቱ የተመዘገበው ዲፕሎማሲያዊ ድል እንዲሁም የባህር በር ማግኘቷ በቀጣናው የሚኖራትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ ከማጉላት አኳያ የሚኖረው ፋይዳም ተዳሷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ኢብራሒም ኢድርስ፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ከሰላም ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት የተጋበዙ እንግዶችም በመድረኩ ተካፋይ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም