ቀጥታ፡

አምስት መቶ ኪሎ ግራም በሚመዝን መዳብ ስርቆት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ))፡- በቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ጉድጓድ ውስጥ ለውስጥ ሁለት ኪሎሜትር በመጓዝ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን መዳብ ሰርቀዋል የተባሉ አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።

ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ጉምሩክ ጀርባ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚት ግቢ ውስጥ ነው ብሏል።

ግለሰቦቹ ከዚህ በፊት በጥናት ላይ የተመሰረተ በተመሳሳይ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ጥርጣሬም እያጣራ መሆኑን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።

ወንጀል በተፈጸመበት ስፍራ ንብረትነታቸው የጉምሩክ ኮሚሽን የሆኑ የተለያዩ ኮንቴይነሮች እንደሚገኙበት ፖሊስ አስታውቋል።

በዚህም ተጠርጣሪዎች አፋ (ኦቼ) የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አካባቢ ከሚገኘው የፍሳሽ ማስወገጃ ጉድጓዳ በመግባት እና ሁለት ኪሎ ሜትር ውስጥ ለውስጥ በመጓዝ የጉምሩክ ኮሚሽን አስቀምጧቸው ከነበሩ ኮንቴይነሮች አንደኛውን በመክፈት 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮፐር ወይም መዳብ ይዘው በፍሳሽ ማስወገጃው ጉድጓድ ሲወጡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም