ቀጥታ፡

በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል

ሐረር፤ ታህሳስ 09/2017 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል ዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ እያደረገ ያለው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ተናገሩ።

በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የ2017 በጀት ዓመት የአባላት ዓመታዊ ዕድሳትና አዳዲስ አባላት ምዝገባ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናውኗል።


 

በመርሃ ግብሩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ዑመር፣ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዷለምን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የወረዳ አመራር አባላት፣ የጤና ባለሙያዎችና ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል።

በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ከ46 ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥም 7 ሺህ 478 የሚሆኑት በመንግስት ወጪ ነፃ የህክምና አገልግሎት ያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአገልግሎት የታቀፉ ከ146 ሺህ በላይ ሰዎች በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውንና 42 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የጤና አገልግሎት ግዢ መፈጸሙን አብራርተዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፍትሃዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ከመስጠትና የመደጋገፍና የመተጋገዝ ዕድሎችን እያሰፋ ያለ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በክልሉ ዘጠኝ የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶችን በመክፈት ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ተናግረዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ፤ ይህን ስራ ለማስፋት ሁሉም አስተዋጽኦውን እንዲያጎለብት ጠይቀዋል።

በክልሉ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ማህበረሰብ በማዳረስ ረገድ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ ናቸው።

በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የተከናወኑት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን በማከል።

ለውጤቱም ወረዳዎችና ባለድርሻ አካላት ያበረከቱት አስተዋጽዎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በ2017 ለሚከናወነው ስራም በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም