ሰላም ፈላጊው ህብረተሰብ ይሄንኑ ጽኑ ፍላጎቱን በሰላም ባጠናቀቀው የድጋፍ ሰልፍ አሳውቋል - የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ህብረተሰቡ ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት በየአካባቢው አደባባይ በመውጣት ባካሔደውና በሰላም ባጠናቀቀው የድጋፍ ሰልፍ አረጋግጧል ሲል የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በነበረው የሰላም እጦት ህብረተሰቡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተዳርጎ ቆይቷል።

ችግሩን ለመፍታት በተቀናጀ መንገድ በተከናወነው የህግ ማስክበር ስራ የተሻለ ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።

መንግስት እየወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር ተልዕኮ ለመደገፍ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የተካሔደው ሰልፍ ላይ በፖሊስና በሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ቅንጅት በተከናወነ ስምሪት ያለምንም ችግር በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ የሰላም መደፍረስ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለው እንደሆነና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለውን ጽኑ ፍላጎትም ባካሔደው ህዝባዊ ሰልፍ ማረጋገጥ እንደቻለ አብራርተዋል።

በቀጣይም የተገኘውን ሰላም አፅንቶ በዘላቂነት ለማስቀጠል ከመላ ህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ መስራት የሁሉም ኃላፊነትና ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያልተቆጠበ ጥረት ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም