የአንካራው ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአንካራው ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ)፦የአንካራው ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን በብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል አስተባባሪ መሐመድ እድሪስ (ዶ/ር ገለጹ።
በተርኪዬ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አቀራራቢነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአገራቱ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
የተደረሰው ስምምነትም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እውን ለማድረግ የሚያስችልና ለቀጣናው ሰላምና የጋራ ልማት ወሳኝ መሆኑ በስፋት ተነስቷል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል አስተባባሪ መሐመድ እድሪስ (ዶ/ር)፤ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት በብዙ መንገድ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለምታነሳው የባህር በር ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ የሚሰጥና ብሄራዊ ጥቅሟንም በዘላቂነት የሚያስጠብቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ጥያቄ ከሀገርም ባለፈ ዓለም አቀፍ አጀንዳ የሆነበትና ተገቢነቱም በብዙዎች ዘንድ የታመነበት ስለመሆኑም ነው ያነሱት።
በመሆኑም የአንካራው ስምምነት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅም ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ የትብብር ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን የማጠናከርና የባህር በር ጥያቄ ምላሽ በሚያገኝበት ሁኔታ ላይ አተኩራ የምትሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የአንካራው ስምምነት የአገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገና ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፤ በአንካራ ያደረጉት ውይይት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበሩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ግንኙነታቸውን ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው።