ሰላምን በመጠበቅ ልማትን እናስቀጥላለን - የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በመጠበቅ ልማትን እናስቀጥላለን - የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

ሰቆጣ ፤ታህሳስ 9/2017 (ኢዜአ)፡- የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ልማትን እናስቀጥላለን ሲሉ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ "ሰላማችን እናፅና ልማታችንን እናስቀጥል "በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ህዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
የሰልፉ ታዳሚዎች ፥ መንግስት ህግ በማስከበር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ሊያስከብር ይገባል፤ መንግስት ለሰላም መስፈን የሚወስደውን እርምጃ እንደግፋለን" የሚሉና መሰል መፈክሮችን በማንገብ ድምጻቸውን አሰምተዋል ።
“ህዝቡ ሰላም ፈላጊ በመሆኑ ሁሉም አካል ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል” ሲሉም አስገንዝበዋል ።
በከተማው የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ አጅጉ አለማየሁ “ በአካባቢው ያለው የሰላም ችግር ህፃናትን ከትምህርት ገበታ ከማስቀረት ባለፈ ህብረተሰቡን ለከፋ ጫና ዳርጓል” ብለዋል።
"እኛ ሰላም እንፈልጋለን፤ ሁሉም የህዝቡን ሰላም ፈላጊነት በመረዳት ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል” ብለዋል።
የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ልማትን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል ።
በሰቆጣ ከተማ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ብርቱካን ገብረ ህይወት በበኩሏ “ሁሉም የሰላም አማራጭን ሊከተል ይገባል” ብላለች።
በአንዳንድ ወረዳዎች ባለው የሰላም ችግር አቻዎቿ ትምህርት ለመከታተል አለመቻላቸውን ጠቁሟ ሁሉም ለሰላም ዘብ በመቆም መፍትሄ እንዲያመጣና ችግሩን ለማስገንዘብ ሰልፍ መውጣቷን ገልጻለች ።
“ሰላም የሁሉም መሰረት በመሆኑ ሁሉም የሰላም ዘብ ሊሆን ይገባል” ያሉት ደግሞ የክልሉ የሰላም ካውንስል አባል ሃጅ ሰለሞን መሃመድ ናቸው።
ሁሉም አካል ለዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል ።
የብሄረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን “ሰላም የሁሉም መሰረት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል” ብለዋል።
መንግስት ለክልሉ ሰላም መስፈን በተደጋጋሚ ባቀረበው የሰላም ጥሪ መሰረት በብሄረሰብ አስተዳደሩ 250 ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ቀደመ ህይወታቸው መመለሳቸውን አመልክተዋል።
አሁንም ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ ሊጠቀሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ህብረተሰቡ ለአካባቢው ሰላም መስፈን እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር "ሰላማችን እናፅና ልማታችንን እናስቀጥል "በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በሁሉም ወረዳዎች ህዝባዊ ሰልፎች ተካሂደዋል ።