ቀጥታ፡

በተለያዩ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ)፦በተለያዩ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ።

ጉባዔው ታህሳስ 11 እና 12 ቀን 2017 ዓም የመጀመሪያውን የሰላም ኮንፈረንስ በድሬደዋ ከተማ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ''ሃይማኖት ለሰላም ለአንድነትና ለመከባበር'' በሚል መሪ ሃሳብ ያካሄዳል።

ይህንኑ ኮንፈረንስ በማስመልከት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የጉባዔው ዋና ጸሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ፤የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ወደ ሰላም መምጣታቸውን በታላቅ ደስታና አድናቆት ተቀብለነዋል ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን እንደ መልካም ምሳሌና ጅማሮ በመውሰድ የአገሪቷን ሰላም የተሟላ ለማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ግጭትና ጦርነት የህዝብን ስቃይ የሚያባብሱ፣ የአገሪቷን ኢኮኖሚ የሚጎዱ ብሎም የመስራትና የመንቀሳቀስ ነጻነትን በመገደብ ለውስብስብ ችግር የሚያጋልጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ህዝቡ ሰላም እንዲያገኝ እና ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ ለማስቻል በድጋሚ የሰላም ጥሪ መቅረቡን ነው ያብራሩት።

በሰላምና በአንድነት ዙሪያ በጋራ ለመምከር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ የታሰበው ኮንፈረንስ ታህሳስ 11 እና 12 ቀን 2017 በድሬዳዋ ከተማ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይከናወናል ብለዋል፡፡



ኮንፈረንሱ በቀጣይ በሁሉም የክልል ከተሞች እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ ህብረተሰቡ የሰላም መሳሪያ እንዲሆን የማንቀሳቀስ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በኮንፈረንሱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ፤ከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፤የአገር ሽማግሌዎች ፤ የድሬደዋ አስተዳዳርና የከተማዋ ነዋሪዎች የሚታደሙ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የህብረተሰቡን ንቁ ተሳትፎና ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ የአገሪቱ ህዝቦች በየአካባቢያቸው ሰላም እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ተሰላፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም