ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የኢንቨስትመንት ፎረም በጁባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ)፡-ሁለተኛው የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የኢንቨስትመንት ፎረም በቅርቡ በጁባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር አባቢ ደምሴ፥ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር አንቶኒ አኮን እና የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ካው ናክ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት የሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።

የድንበር አስተዳደርን በማሻሻል እና የሁለቱን እህትማማች አገራት ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ወጥ የሆነ የአሰራር ማዕቀፍ ማበጀት እንደሚገባ አንስተዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በጁባ በቀጣይ የሚካሄደውን የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ኢንቨስትመንት ፎረም አስመልክቶ መነጋገራቸውን በጁባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር አንቶኒ አኮን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ጽንሰ ሀሳቦች ፀንተው እንዲቀጥሉ እየተወጣች ያለውን ሚና አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ እያደረገች ላለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም