በትግራይ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና መሰጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና መሰጠት ተጀመረ
መቀሌ፤ ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በ451 ትምህርት ቤቶች ዛሬ መሰጠት ተጀምሯል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ተወካይ አረጋዊ ዘፈሩ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በተሳለጠ የትምህርት ፕሮግራም ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 26 ሺህ 156 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ለፈተና ተቀምጠዋል።
ከተፈታኞቹ መካከል 50 በመቶ ያህሉ ሴቶች እንደሆኑም ተወካዩ ገልጸዋል።
የተማሪዎቹ የፈተና ውጤት በአምስት ቀናት ውስጥ እንደሚገለጽ አመልክተው ወደ ዘጠነኛ ክፍል ማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች በቀጥታ የ9ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ተናግረዋል።
እየተሰጠ ያለውን የ8ኛ ክፍል ፈተና በመቀሌ ባሉ ሁለት ትምህርት ቤቶች ተገኝተው ያስጀመሩት የትምህርት ቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ስማዒል ዓብደሩሕማን ናቸው።
ፈተናውን እየወሰዱ ያሉ ተማሪዎች በበኩላቸው ከፈተናው ባለፈ ለቀጣይ የትምህርት ደረጃቸው ጭምር የሚያግዝ ዝግጅት አድርገው ወደ ፈተና መግባታቸውን ገልፀዋል።