በጎንደር ከተማ ሰላምን ማጽናት የህልውና ጉዳይ ነው - አቶ ቻላቸው ዳኘው

ጎንደር፤ ታህሳስ 9/2017(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ ሰላምን በማጽናት ልማትና ብልፅግናን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ሰላምና ልማትን የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ አካሂደዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው በሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የጎንደር ከተማ ሕዝብ የሰላም ደውል ጎንደር ላይ ደውሏል፤ ይህ ደውል የከተማችን ሰላም፣ ልማትና ተስፋ ነው ብለዋል።

ጎንደር ሰላም ብታጣ ተጎጂዎች እኛ ነን፤ የዚህ ከተማ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግናን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።


 

የከተማዋን ሰላም ለማጽናት ሌት ተቀን ያለረፍት እየሰራን ነው ያሉት አቶ ቻላቸው፤ የጽንፈኝነትና የህገ ወጥነት እሳቤ ተገቢነት እንዳሌለው ተናግረዋል።

መንግስት የጎንደር ከተማን ህብረተሰብ የመልማት ጥያቄ በሚመልስ መንገድ የተለያዩ የግንባታ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

ከጎንደር አዘዞ ኤርፖርት የኮሪደር ልማት፣ የታላቁ አብያተ መንግስታት ግብረ ህንጻ ጥገናዎች፣ የመገጭ ግድብና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በመጥቀስ አብራርተዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በፋሲለደስ ስታዲየም ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ ክልላችንና ከተማችን የሚያስፈልገው ጦርነት ሳይሆን ልማትና ሠላም ነው ብለዋል።

መንግስት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እንደግፋለን፣ የመከላከያ ሠራዊቱና የክልሉ የጸጥታ ሀይል ለሠላም መስፈን እየከፈሉት ላለው መስዋዕትነት ክብር እንሰጣለን ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም