ኢትዮጵያ በአጀንዳ 2063 ማዕቀፍ ውስጥ … - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአጀንዳ 2063 ማዕቀፍ ውስጥ …
የአፍሪካዊያን የግማሽ ምዕተ ዓመት መዳረሻ ግብ ነው-አጀንዳ 2063። በአውሮፓዊያኑ 2013 ተፀንሶ፤ በ2015 በአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባዔ ጸድቋል።
በአውሮፓዊያኑ ግንቦት 25 ቀን 1963 የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዲስ አበባ ውስጥ በተመሰረተበት ዕለት የአፍሪካ አባት የሚሰኙት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር“እኛ አፍሪካውያን በዓለም ጉዳዮች እና ዓለም እንዴት መጓዝ አለባት? በሚለው የሀሳብ መንሸራሸሮች ውስጥ ሚና ሊኖረን ይገባል። እኛ አፍሪካውያን ነፃነት ብቻ ሳይሆን አንድነት እንሻለን” ብለው ነበር።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች አባቶች በወቅቱ ያቀነቀኑት እሳቤ ዛሬ ገቢራዊ ለማድረግ ጥረት ተጀምሯል። በአውሮፓዊያኑ መስከረም 9 ቀን 1999 በሊቢያ ባካሄደው የመሪዎች ስብስባ የድርጅቱን ስያሜ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲለወጥ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተደረሰ። ከሶስት ዓመታት በኋላ 2002 በደርባን(ደቡብ አፍሪካ) በነበረው ስብሰባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ‘አፍሪካ ሕብረት’ ተሰኘ።
ኅብረቱ ከፖለቲካ ውኅደት በተጨማሪ አህጉራዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚ ልማትና ትስስር ለማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው። በአውሮፓዊያኑ ጥር 2015 በአዲስ አበባው በተካሄደው 24ኛው የሕብረቱ መሪዎች ጉባዔም ይህን ህልም ዕውን ለማድረግ የተቀረጸው አጀንዳ 2063 ጸደቀ።
“የምንፈልጋት አፍሪካ” የሚል መሪ ሀሳብ ያነገበው የግማሽ ምዕተ ዓመቱ ዕቅድ ‘አጀንዳ 2063’ ሰባት ዋነኛ ዓላማዎችን አቅፏል። ዓላማዎቹን ጠቅለል ስናደርጋቸውም፤
በሁሉ አቀፍ ዕድገትና ልማት የበለጸገች፤ የተሳሰረችና ፖለቲካዊ አንድነት ያላት፤ መልካም አስተዳደር የሰፈነበት፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት የሚከበርባት፣ ፍትሕ የነገሰበትና ዴሞክራሲያዊት እና አንድነቷ የተጠበቀ አፍሪካን ዕውን ማድረግ ነው።
እንዲሁም ጠንካራ የባህል ማንነት፣ የጋራ ቅርስና እሴቶችና ማህበረሰባዊ የሞራል መሰረት ያላት፤ ሁሉንም ዜጎች ያማከለ አካታች ልማት እና ጠንካራ፣ የማይበገርና በዓለም መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪካን ዕውን ማድረግ የሚሉት ዓላማዎች ናቸው።
የበይነ-አፍሪካ በመሰረተ ልማት መዘርጋት፣ ነጻ ገበያ እና የጋራ የመገበያያ ገንዘብ፣ የሕብረቱን ተቋማዊ ቁመና ማጠናከር እና ስራ አጥነት ምጣኔን መቀነስ የአጀንዳ 2036 ግቦች ናቸው።
አጀንዳ 2063ን ዕውን ለማድረግ ሀገራት የአጀንዳውን ግቦች ከብሔራዊ የዕድገትና የልማት ዕቅዶቻቸውን ጋር ማስተሳሰር ይጠበቅባቸዋል። የሀገራት የልማት ጥረቶችም በዚህ ቅኝት መቃኘት ግድ ይላቸዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አጀንዳ 2063 ማዕቀፍ አንጿር ቁመናዋ ምን ይመስላል የሚለውን እንቃኝ።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት፣ በቀጣናዊ ትስስር፣ በግብርና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥረቶቿ ለአጀንዳ 2063 ስኬት የሚያግዙ ናቸው።
ከአየር ንብረት ለውጥን መከላከል እና ምቹ ከባቢ ከመፍጠር አኳያ ኢትዮጵያ ላለፉት ስድስት ዓመታት ገቢራዊ እያደረገች ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እስካሁን 40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተክላለች። ጎረቤት አገራትንም ችግኝ በመላክ ተጠቃሚ አድርጋለች። ይህን ኢኒሼቲቭ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የአረንጓዴ አሻራን የቀጣናው ቁልፍ ፕሮጀክቶች አድርጎታል።
የአፍሪካ ሕብረት ደግሞ አረንጓዴ አሻራ የሰሃራ በርሃን መስፋፋት ለመግታት እንደ አፍሪካ እየተተገበረ ያለውን ታላቁ የአረንጓዴ ግድግዳ(ግሬት ግሪን ዎል) ዓላማ ጋር ለማስተሳሰር እየሰራ ነው። በርግጥ አረንጓዴ አሻራ በዓለም መድረክም ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተቸረው መርሐ ግብርም ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ በታዳሽ ሃይል ላይ አተኩራለች። በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለመተካት ፖሊሲ ቀርጻ አበክራ እየሰራች ነው። የግሉ ዘርፍ ተዋኒያን በዚህ ዘርፍ በስፋት እየተሳተፉ ነው። እንደ ሀገር በቀጣይ 10 ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል። በአዘርባጃን ባኩ በተካሄደው 29ኛው የመንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ድምፅ ብቻ ሳትሆን ለአፍሪካን ዘላቂ ጥቅምና ፍላጎት ለማረጋገጥ የመሪነት ሚናዋን እንደምትውጣ ገልጻለች።
በአጀንዳ 2063 ግቦች መካከል አንዱ በሆነው በመሰረተ ልማት ትስስር አኳያ ኢትዮጵያ ለጂቡቲ፣ ለኬንያና ለሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች ነው። ሌላው ቀጣናዊና አህጉራዊ አንድምታ ያለው ግዙፉን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ታዳሽ ኅይል ፕሮጀክት እያጠናቀቀች ነው። ለታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በሂደት ላይ ትገኛለች።
በባቡር መሰረተ ልማት እና በመንገድ መሰረተ ልማት ከጎረቤቶቿ ጋር እየተሳሰረች ነው። በፈጣን መንገድ፣ ባቡርና በሌሎች ግዙፍ መሰረተ ልማቶች አማካኝነት ኢትዮጵያ፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርት የሚያስተሳስረው የ"ላፕሴት ፕሮጀክት" ሌላው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር መጠናከር የምትሳተፍበት ፕሮጀክት ነው።
በአፍሪካ ያሉት ከ65 በላይ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን እያስተሳሰረ ነው። ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካ እሳቤ የበይነ-አፍረካዊያን ሁሉን አቀፍ ትስስርና ትብብር እንዲጎለብት እየሰራች ነው።
በሰላምና ጸጥታ ረገድ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ወታደሮችን በማሰማራት ግንባር ቀደም ሀገር ናት። በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ ላይበሪያ፣ በሱዳንና በሶማሊያ ወታደሮቿ ተሰማርተው ለአፍሪካ ሰላም መስዋዕትነት ከፍለዋል።

ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የተመድ መስራች አፍሪካዊት ሀገር ናት። ዛሬም አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ እየታገለች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዓለም የባለብዙ ወገን መድረኮች ሁሉ የአፍሪካ የፍትሀዊ ጥያቄ ውክልና ይገባኛል አቋም ሲያንጸባርቁ ተደምጠዋል። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጉዳይ ያላት ወገንተኝነት ለአህጉሪቷ መጻዒ መዳረሻ ጋር የተናበበበ ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ነው።
የ2063 አጀንዳ አካል የሆነው የግብርና ዘርፉን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ከማስፋት አኳያም ኢትዮጵያ በርካታ ተጨባጭ ተግባራት እያከናወነች ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ለአብነትም በሌማት ትሩፋትና በሰብል ምርት የሰራቻቸው ሥራዎችና ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ለአጀንዳው መሳካት የራሱን አስተዋጽዖ የሚያደርግ ነው።
በስንዴ ምርታማነት በማሳደግ ራሷን ከመቻል አልፋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችላለች። የወተትና የዶሮ ምርታማነት ጨምራል። በዚህ ዘርፍ የተመዘገበው እመርታ ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አንድምታ ያለውና አህጉራዊ ተቋማትም ዕውቅና የቸሩት ጉዳይ ነው።
አዲስ አበባን ጨምሮ የከተሞች ኮሪደር ልማትም ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማት በአህጉሪቱ ለማምጣት የሚደረገውን የ2063 አጀንዳ ጥረት የሚያግዝ ነው።
ዘመናዊ፣ ለኑሮ ምቹ፣ ውብ እና አካታች የዜጎች ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ እየተከናወነ ነው። ይህ ደግሞ የአፍሪካዊያን መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መታየቱ፤ ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያንም ተስፋና ቁም ነገር የሚያስጨብጥ ነው። ከአጀንዳ 2063 ዕቅዶች ጋር ተሰናስኖ ከተሞች የእድገት መሰላል ይሆኑ ዘንድ ወሳኝ መልዕክት ይቀሰምበታል።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች የምታደርጋቸው ስራዎችና ከአጀንዳ 2063 ማዕቀፍ ጋር የሚጣጣሙና ለትግበራው ስኬት የሚያግዙ ናቸው። ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በብሔራዊ ፖሊሲዎቻቸው አካተው ከሰሩ አጀንዳ 2063 ይሳካል። የቀድሞ የአፍሪካ አባቶች ራዕይም ዕውን ይሆናል።