ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጎልበት ቁርጠኛ ናት- አምባደር እሸቴ ጥላሁን

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 08 /2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር በተለያዩ ትብብር መስኮች ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ገለፁ።

በቤልጂዬም፣ ኔዘርላንድስ፣ ሉክሰምበርግ እና በአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ከአውሮፓ ሕብረት የስደት እና የውስጥ ጉዳዮች ምክትል ዳይክተር ጀኔራል ጆሃንስ ሉችና(ዶ/ር) ጋር በብራሰልስ ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ በፍልሰተኞችና ስደት ተመላሾች እንዲሁም በልማት ጉዳዮች የሁለትዮሽ ትብብር እንዲጎለብት ያደረገችው በጎ ጥረት በውይይቱ ላይ ተወስቷል።

አውሮፓ ሕብረት ለስደት ገፊ መንስዔዎችን ከመቅረፍ ባሻገር ተመላሽ ስደተኞችን ለመደገፍ ያሳየው ቁርጠኝነት ተነስቷል።

አምባሳደር እሸቴ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ያላትን ዝግጁነት አጽንኦት ሰጥተው አረጋግጠዋል።

የቪዛ ገደብ በንግድና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ የሚያሳድረውን ጫና በተመለከተም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

በስተኞች፣ ተመላሾችና በሌሎች የጋራ ጥቅሞች ዙሪያ ግልጽና ገንቢ ውይይቶችን ለመቀጠልም ሃላፊዎቹ ተግባብተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አምባሳደር እሸቴ በአውሮፓ ሕብረት የቻይና ሚሲዮን መሪ ከሆኑት አምባሳደር ካይ ራን ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር እሸቴ ቻይና በተለያዩ መስኮች ለኢትዮጵያ ማህበረ-ምጣኔ ሀብታዊ ግስጋሴ የነበራት ወሳኝ ሚና እና ድጋፍ በማውሳት አድንቀዋል።

አምባሳደር ካይ ራን በበኩላቸው ሀገራቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ኢንዱስትሪ ልማት ዕውን እንዲሆን ትብብሯን ታጠናክራለች ብለዋል።

የንግድ፣ ኢንቨስመንትና መሰረተ ልማትን ጨምሮ በተለያዩ ኢኮኖሚ መስኮች ያለው የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት እየጎለበተ መምጣቱን አውስተዋል።

አምባሳደሮቹ በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የሚያደርጓቸውን ምክክሮች ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስቀጠል ያላቸውን መሻት መግለጻቸውን ብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም