ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን ከዩናይትድ ኪነግደም ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ኤሚሊ ቶርንቤሪ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ብሩክ ለሰብሳቢዋ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊስ እና አገራዊ ምክክርን ጨምሮ በተለያዩ ኢኒሼቶቮች ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እያደረገች የምትገኘው ጥረት ተዳሷል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያዎችን ጨምሮ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠራቸውን አመልክተዋል።

ሁለቱ ወገኖች የአገራቱን ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ትብብር በማጠናከር ትስስራቸውን ይበልጥ የተቀራረበ ለማድረግ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም