የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ጥቅምን እያስገኘ ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ጥቅምን እያስገኘ ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 8/2017(ኢዜአ)፦ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር “ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ” አርሶ አደሮች ቡናቸውን ለዓለም በማስተዋወቅ ገበያቸውን እንዲያሳድጉ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።
የ2024 የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር“ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ” አሸናፊ ለሆኑ 40 አርሶ አደሮች ዕውቅና የማበርከት መርሀ ግብር በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት ርእሰ-መስተዳድሩ ውድድሩ አርሶ አደሮች ቡናቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያስተዋውቁና ተፈላጊነቱ እንዲያድግ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
በዚህ ውድድር አርሶ አደሩና በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው ለኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሪ ማስገኘታቸውን አስረድተዋል።
በውድድሩም የሲዳማ ክልል ጥራት ያለው ቡና ማቅረቡን ጠቅሰዋል።
በውድድሩ የተሳተፉ አርሶ አደሮችም ኢኮኖሚያቸውን ከማሳደጋቸውም በላይ ወደ ላኪነት በመሸጋገር ተጨማሪ ሀብት እያፈሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የቡና ምርት የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችለው የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ አመታት ለተግባራዊነቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።
ከእነዚህ ተግባራት ውስጥ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ተጠቃሽ እንደሆነ ገልፀው የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ላይ በመጠን፣ በጥራትና በገቢ ከፍ እያለ እንዲመጣ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
የውድድሩ አሸናፊ አርሶ አደሮች ቡናቸው በዓለም አቀፍ ጨረታ ተወዳድሮ ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኙ በቀጥታ ወደ ውጭ የሚልኩበትን ፈቃድ አግኝተው ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ ከክልሉ መንግስት ጋር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ለውድድሩ ስኬታማነትና ለተገኘው ውጤት የየራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ባለድርሻ አካላትንም አመስግነዋል።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በውድድሩ አሸናፊ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል 34ቱ ከሲዳማ ክልል መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ በአሁን ወቅት የቡና ምርታማነት በሄክታር 11 ኩንታል መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ይህንን መጠን ወደ 15 ኩንታል ለማድረስ በዕቅድ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ዕውቅና ከተሰጣቸው 40 አርሶ አደሮች መካከል ከ90 በመቶ በላይ አፈፃፀም ያላቸው ሁለት አሸናፊዎች የዋንጫ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን አስተዋፅዖ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላትም ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።