በባንክ ዘርፉ ከሚሰበሰበው ሃብት 10 በመቶው ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚገኝ ነው - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
በባንክ ዘርፉ ከሚሰበሰበው ሃብት 10 በመቶው ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚገኝ ነው - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 8/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፉ ከሚሰበሰበው ሃብት 10 በመቶው ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚገኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
አቶ ማሞ ይህን ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ11ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና የባንክ ሥራ ማሻሻያ አዋጅን ሲያጸድቅ ነው።
የባንክ ሥራ አዋጁ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን በተመለከት ምን ይዞ መጣ ለሚለው የምክር ቤት አባላት ጥያቄ የባንኩ ገዥ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ጊዜ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ መንግስት ካደረጋቸው መሰረታዊ ለውጦች አንዱ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን መፍቀድ ነው ብለዋል።
ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የእስልምና እምነት ተከታዮች በፋይናንስ አካታችነት መርህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንም ነው ያነሱት።
በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ራሳቸውን የቻሉና ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች መቋቋማቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ መደበኛ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ራሱን የቻለ ቅርንጫፍና መስኮት ከፍተው ከወለድ ነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ መፈቀዱ ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፉ ከሚሰበሰበው ሃብት 10 በመቶው ከወለድ ነጻ የሚገኝ እንደሆነም ተናግረዋል።
ዛሬ በጸደቀው የባንክ ሥራ አዋጅ ከወለድ ነጻ አገልግሎትን በተመለከተ በግልጽ የተቀመጠ ድንጋጌ መኖሩንም አንስተዋል።
ብሔራዊ ባንክ ባንኮች የሸሪዓ ህግን ተከትለው የሚሰሩበትን ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የቁጥጥር መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል መቀመጡንም ገልጸዋል።