የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የ49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለበት ኤር ኮንጎ ሥራውን በይፋ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የ49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለበት ኤር ኮንጎ ሥራውን በይፋ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ታህሰሥ 8/2017(ኢዜአ)፦ የዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ አየር መንገድ ኤር ኮንጎ ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ተካሄደ።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ተገኝተዋል።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ባለፈው ኅዳር 2017 ዓ.ም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኤር ኮንጎ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤር ኮንጎ 49 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ የዶሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ መንግሥት ደግሞ የ51 በመቶ ድርሻ አለው።
ኤር ኮንጎ በሁለት ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች በአሕጉሪቱ ውስጥ ባሉ ሰባት ኤርፖርቶች በረራ በማድረግ ነው አገልግሎቱን የጀመረው።
ይህ ጥምረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2035 አንዱ አካል ሲሆን ከዚህም በፊት በሎሜ አስካይ አየር መንገድ፣ በሊሎንግዌ የማላዊ አየር መንገድ እንዲሁም በሉሳካ የዛምቢያ አየር መንገድን በጋራ ማቋቋሙ ይታወሳል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር ውል በመፈጸም በጋራ ይሰራል።