ቀጥታ፡

የአስራ አንድ ዓመት ሕፃን ልጅ በማገት 4 ሚሊዮን ብር የጠየቀው ተጠርጣሪ ተያዘ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 8/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ የ11 ዓመት ሕፃን ልጅ በማገት ወደ ሸገር ከተማ አምጥቶ 4 ሚሊዮን ብር የጠየቀውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

አበራ አላዩ የተባለው ግለሰብ ከሚኖርበት ሸገር ከተማ በመነሳት አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ዎኮ ፍቅረሰላም ቀበሌ ከሚኖር ገብረመድህን አላዩ ከተባለ ወንድሙ ጋር በመሆን ህዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 4:30 ሰዓት እገታውን መፈፀማቸው ተገልጿል፡፡


 

ድርጊቱንም በወረዳው ለሚ ከተማ የሚገኘውን አውሌ ገብሩ የተባሉ ግለሰብን መኖሪያ ቤት ሰብረው በመግባት ጥይት ተኩሰው በማስፈራራት የታጋቹን እናትና እህቶቹን እጅ በገመድ በማሰር ሕፃን ባሳዝነው አውሌን አግተው መውሰዳቸው ተመላክቷል፡፡

ሕፃኑንም ለሦስት ቀናት ዋሻ ውስጥ በማሳደር ይዘው በእግር እስከ ፍቼ ከተጓዙ በኋላ ሁለተኛው አጋች ገብረመድን አላዩ ወደ አማራ ክልል መመለሱም ተገልጿል፡፡

ከዚያም አጋቹ ሕፃኑን ህመምተኛ በማስመሰል በብርድ ልብስ በመሸፈን በሕዝብ ትራንስፖርት ከፍቼ ከተማ ወደ ሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ በማድረስ በተከራየው መኖሪያ ቤት ውስጥ በመደበቅ ለሕፃኑ አባት ስልክ በመደወል 4 ሚሊየን ብር እንዲከፍል ጠይቋል ነው የተባለው።


 

ይህ ካልሆነ ግን ሕፃኑን በሕይወት እንደማያገኘው በማስፈራራት ላይ እንዳለ ጉዳዩን የሰማው አዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው የሕፃኑ አጎት ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃውን ማድረሱም ተገልጿል።

በዚህም ፖሊስ መረጃውን መነሻ በማድረግ ተጠርጣሪውን ተከታትሎ በተከራየው መኖሪያ ቤት ውስጥ ከተባባሪ ባለቤቱ ጋር እጅ ከፍንጅ በመያዝ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም