ቀጥታ፡

የእስራኤል ባለሀብቶች ለግሉ ዘርፍ ክፍት በሆነው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2017(ኢዜአ)፦ የእስራኤል ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ለግሉ ዘርፍ ክፍት በሆነው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው እስራኤሉ አስሆልዲንግ ኩባንያ ባለቤቶች ጋር ተወያይተዋል።

አቶ በርኦ ለኩባንያው ባለቤቶች የኢትዮጵያን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ የኢንቨስትመንት አማራጮች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የሰው ኃይል፣ ማበረታቻዎች እና ሌሎች በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ አመልክተዋል።

ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኩባንያው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ የአገራቱን ለረጅም ጊዜ የቆየ የሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክራል ነው ያሉት።

የአስሆልዲንግ ኩባንያ ባለቤቶችም ኩባንያው በሎጂስቲክስ፣ በግብርና፣ በእንስሳት ልማት፣ በኢነርጂ፣ በሳይበር እና በሌሎችም ዘርፎች ከተለያዩ አገራት ጋር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያም በተለያዩ አማራጮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም