ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 8/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደረሱ።
ሁለተኛው የኢትዮጵያና የኅብረት የስትራቴጂክ አጋርነት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገርና በአዲስ አበባ የሚገኙ 21 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በውይይቱ ማጠናቀቂያ ኢትየጵያና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
ውይይቱ የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
ተወካዮቹ ሽብርተኝነትን መዋጋት ጨምሮ ቀጣናዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና መልሶ ግንባታ፣ ኢኮኖሚ፣ ልማት፣ ፋይናንስ፣ ንግድ እና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የባለብዝሃ ወገን ማዕቀፍ ትብብር ውይይት የደረገባቸው አጀንዳዎች ናቸው።
በውይይቱ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት የሁለትዮሽ ትብብራቸው እና የሀሳብ ልውውጦችን የሚያጠናክሩ ጥረቶችን ለማድረግ መስማማታቸውን በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት ስትራቴጂክ አጋርነት መድረክ እ.አ.አ በ2023 መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ ተገልጿል።
የአጋርነት መድረኩ መካሄድ የጀመረው ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የሳሞአ ስምምነትን ከፈረሙ በኋላ ነው።
የአውሮፓ ኅብረት በራሱ ማዕቀፍ እና የኅብረቱ አባል አገራት ከኢትዮጵያ ጋር በፈረሟቸው ስምምነቶች አማካኝነት ሀገሪቷ የፋይናንስ ድጋፎችን እያገኘች እንደምትገኝ መግለጫው አትቷል።
ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2016 የስትራቴጂክ አጋርነት ትብብር መፈራረማቸው ይታወቃል።