ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ነባራዊ ሀገራዊ ዕድገትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሻሻል ነው

አዳማ፤ ታህሳስ 8/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ አሁናዊ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት በሚመጥን እና የሀገሪቷን የወደፊት ጉዞ ታሳቢ ባደረገ አግባብ ሊሻሻል መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የተሻሻለ ሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ለማዘጋጀት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲው የሕዝብ ዕድገትን ለልማትና ዕድገት ለማዋል፣ ልማትና ዕድገትን ለማፋጠን ወሳኝ ሚና አለው።

ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በስራ ላይ የሚገኘው ነባሩ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እንደተገኘበት ተናግረዋል።

የትምህርትና ጤና ዘርፎችን ጨምሮ ለሕዝብ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ማስተሳሰር፣ ለመቆጣጠርና ለተመጣጣኝ መሰረተ ልማት ዝርጋታ አስታዋጽኦ ስለማድረጉም አንስተዋል።

ያም ሆኖ ፖሊሲው ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑ አሁናዊውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች በሚመጥን አዲስ ፖሊሲ ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ገልጸዋል።

በመሆኑም ከፖሊሲ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ የሲቪል ማህበራትና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትና የውጭ ተሞክሮ ግብዓት ተካቶበት እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል።

በስራ ላይ ከሚገኘው የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ዝግጅት የተሳተፉት ፕሮፌሰር ንጉሴ አበራ እንደገለፁት፤ ፖሊሲው በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማት፣ በግብርና በሌሎች ዘርፎች ዘርፈ ብዙ ውጤት አስገኝቷል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የልማትና ዕድገት ምዕራፍ እንዲሁም የሕዝብ ቁጥር ያማከለ እንዲሆን የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲው ማሻሻያ ሊደረግበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፈው ዓመት ጀምሮ የፖሊሲው ማሻሻያ ቅድመ ዝግጅቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች መካከል አቶ ውብሸት ተመስገን፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም